ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በመጀመሪያ የሜዳ ላይ ጨዋታው ሃዋሳን ገጥሞ ነጥብ ተጋርቷል

በግዙፉ የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ያለግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች በአንፃራዊነት ብልጫ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ተጋጣሚያቸው ሃዋሳ ከተማዎች ደግሞ ጥንቃቄ የታከለበት ጨዋታ አከናውነዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ለቡድኑ ተጨዋቾች በስማቸው የታተመ መለያ እና የትጥቅ መያዧ ሻንጣ በስጦታነት ያበረከቱ ሲሆን የደጋፊዎች ማህበሩ ደግሞ ለተጋባዦቹ ሃዋሳ ከተማዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል በማድረግ የጣና ሃይቅን የሚያሳይ ምስል የታተመበት ፎቶግራፍ እንዲሁም አገልግል በባህር ዳር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አማካኝነት በስጦታነት አበርክተዋል።

በሚገርም የደጋፊዎች ድባብ የተጀመረው ጨዋታ እንደ ድባቡ ሞቅ ብሎ ያልቀጠለ ሲሆን ባህር ዳር ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ ተጋባዦቹ ሃዋሳ ከተማዎች ደግሞ በቀጥተኛ አጨዋወት ቀርበዋል። ባህር ዳሮች በሦስተኛ ሳምንት ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ሲዳማ ቡናን ከገጠመው ቋሚ አስራ አንዳቸው ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ የቀኝ መስመር ተከላካያቸውን ሳላምላክ ተገኝን እና የአጥቂ መስመር ተጨዋቻቸውን ፍቃዱ ወርቁን በተስፋሁን ሸጋው እና ቢን አህመድ ዋቴራ ተክተው ገብተዋል። በሃዋሳዎች ደግሞ አስጨናቂ ሉቃስን እና ጸጋአብ ዮሴፍን በአክሊሉ ተፈራ እና ሄኖክ ድልቢ በመተካት ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ለመቆጣጠር ብዙውን ጊዜያቸውን በመሀለኛው የሜዳ ክፍል አሳልፈዋል። እስራሄል እሸቱን በብቸኛ አጥቂነት ያሰለፉት ሃዋሳዎች በጨዋታው ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ለማድረግ 23 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ብሏቸው ነበር። በዚህ ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረው ረጅም ኳስ ተጨራርፎ እስራኤል እግር ላይ ሲደርስ እስራኤል ኳሷን ወደ ግብነት ለመቀየር አልሞ ቢሞክርም ኢላማዋን በመሳቷ ወደ ውጪ ወጥታለች። ብዙ ሙከራዎች ያላስተናገደው የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ በተሰነዘረ ሌላ የሃዋሳ ከተማዎች ሙከራ ግብ ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበር። ሙከራው እንደ መጀመሪያው ሁሉ ከቅጣት የተሻገረውን ኳስ ሄኖክ ድልቢ በግንባሩ ሞክሮት ወደ ውጪ ሲወጣ የታየ ነበር። በመጀመሪያዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች ላይ በነበረው የመሃል ሜዳ ላይ ፍትጊያ ተቸግረው የኋላ ኋላ ግን ብልጫ ወስደው የተንቀሳቀሱት ባህር ዳሮች የሚያገኙዋቸውን ኳሶች ወደ መስመር በማውጣት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም የመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ ሲደርሱ በሚያሳዩት ደካማ የውሳኔ ችግር ፍሬ ማፍራት ተስኗቸው ታይቷል።

ሃዋሳዎች ብልጫ ከተወሰደባቸው በኋላ በመልሶ ማጥቃት የተጫወቱ ሲሆን በ44ኛው ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ብቃቱን ባሳየው በእስራኤል እሸቱ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥረው ምንተስኖት አሎ አክሽፎባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠ የጭማሪ ደቂቃ ላይም ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች በቢን አህመድ ዋቴራ የመቀስ ምት መሪ ሊያደርጋቸው የሚያስችላቸውን ዕድል ቢፈጥሩም ግዙፉ አጥቂ የመታት ኳስ ኢላማዋን በመሳቷ ግብ ሳትሆን ቀርታ ሁለቱም ቡድኖች ያለ ግብ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በእረፍት ሰዓት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊ ማህበር አስተባባሪዎች ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉ ግለሰቦች የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተው ስታድየም ከገባው የስፖርት ቤተሰብ መዋጮ በመሰብሰብ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ታይተቷል።

ከእረፍት መልስ የቀጠለው ጨዋታው ከመጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ በተለየ መልክ በመቀጠል ሙከራዎችን በፍጥነት ሲያስተናግድ ተስተውሏል። ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ከወሰኑ ዓሊ የመዓዘን ኳስ ኤልያስ አህመድ ጥሩ ሙከራ በግንባሩ አድርጎ ባህር ዳርን ቀዳሚ ለማድረግ ቢጥርም ኳሷ ኢላማዋን በመሳቷ ወደ ውጪ ወጥታለች። አሁንም ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በፍቅረሚካኤል አለሙ በተመታ ረጅም ኳስ ግብ ለማግኘት የጣሩ ሲሆን ተክለማርያም ሻንቆ ኳሷን ወደ ውጪ በማውጣቱ ኳሷ መረብ ላይ ሳታርፍ ቀርታለች።

ሃዋሳዎች በተሰነዘረባቸው ሁለት አስደንጋጭ ሙከራዎች የተደናገጡ ቢመስሉም በ54ኛው ደቂቃ የመልስ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በአጥቂ መስመር ተጫዋቾቻቸው ደስተኛ የማይመስሉት ባህር ዳሮች በ61ኛው ደቂቃ ሁለት የአጥቂ መስመር ተጨዋቾቻቸውን (ግርማ ዲሳሳ እና ቢን አህመድ ዋቴራን) በማስወጣት ጎል ለማስቆጠር ተንቀሳቅሰዋል። ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ በመሃል ሜዳ ተጫዋቻቸው ኤሊያስ አህመድ ሁለት ተከታታይ ሙከራዎችን በ65 እና 68ኛው ደቂቃ ቢሰነዝሩም ግብ ለማስቆጠር ግን አልቻሉም። እነዚህ ሁለት ሙከራዎች ከተደረጉ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ባህር ዳሮች ሌላ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢያገኙም የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል አለሙ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የሃዋሳ ከተማዎች ማፈግፈግ የጠቀማቸው የሚመስሉት ባህር ዳሮች አሁንም ግብ ለማስቆጠር ጥረው በ77ኛው ደቂቃ ከፍቃዱ የተሻማውን ረጅም ኳስ ወሰኑ ለዳንኤል አቀብሎት(cut back pass) ዳንኤል አምክኖታል። የሚሰነዘርባቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶችነን በመቋቋም ጨዋታቸውን የቀጠሉት ሃዋሳዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። ተቀይሮ የገባው ብሩክ በየነ ቡድኑን ሶስት ነጥብ ሊያስገኝ የሚያስችል የመጨረሻ ደቂቃ ሙከራ ያደረገ ተጨዋች ሲሆን ተጨዋቹ የመታት ኳስ ብዙም ስራ ሳይበዛበት ጨዋታውን ያጠናቀቀው ምንተስኖት አሎ አምክኗታል። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ ፡LINK