ሪፖርት | ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ያለግብ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

የዕለቱ ተጋጣሚዎች በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን አሳልፈው ነበር የተገናኙት። ፋሲል ከነማዎች ከሀዋሳው የ3-1 ድል አብዱራህማን ሙባረክ እና ከድር ኩሊባሊን በማሳረፍ ያስር ሙገራው እና ሀብታሙ ተከስተን የተጠቀሙ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ ደደቢትን 2-0 ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ አምበሉ አማኑኤል ዮሃንስን በማስገባት ሳምሶን ጥላሁንን አሳርፈዋል። 

በደመናማ የአየር ፀባይ በጀመረው ጨዋታ  በፋሲል ከነማ  በኩል ተደጋጋሚ ወደ ግብ  የመድረስ ዕድሎችን ያስመለከተ ነበር። ፋሲሎች በራሳቸው ሜዳ ኳስ በመመስረት የተሻለ ብልጫ ወስደው  በመጫወት በ3ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ሱራፌል ዳኛቸው ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ቢያሻማውም በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ተገጭቶ ወጥቷል። 12ኛ ደቂቃ ላይ  ኤዲ ቤንጃሚን ከሳጥን ውጭ  አክርሮ የመታው እና በድጋሜ 13ኛ ላይ ያስር ሙገራው ከሳጥን ውጭ የሞከረዉ ኳስ ደግሞ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ። 

በሌሎች ሙከራዎች 26ኛ ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዓለሙ በግራ መስመር ወደ የፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ገብቶ የሞከረው እንዲሁም 27ኛ ላይ ሰዒድ ሁሴን ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል እክርሮ የመታውን ኳስ ደግሞ በዋቴንጋ ኢስማ ተመልሰዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል 11ኛው ደቂቃ ላይ የሰዒድ ሁሰን መዘናጋት ተከትሎ  የተገኝውን ኳስ አቡበከር ነስሩ ቢደርስበትም ሚኬኤል ሳማኪ ቀድሞ  አድኖበታል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ 23ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከአስራ ቱንጆ አሻግሮለት የሞከራቸው በ33 እና 40ኛ ደቂቃዎች ላይም ሌሎች ሙከራዎቹ በግብ ጠባቂ የተመለሱበት የቡናማዎቹ የፊት አጥቂ ሱሌይማን ሎክዋ ነበር። 

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ተሻሽለው የገቡት ቡናዎች የፋሲልን የመሀል ሜዳ ብልጫ ተቋቁመው ነበር የጀመሩት። ጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ ትኩረት ያደረገ እንዲሁም ግጭት የበዛበት ጨዋታም ሆኖም የታየ ነበር። በዚህም የተነሳ ከኢትዮጵያ ቡና በኩል አህመድ ረሺድ  እና አስራት ቱንጆ ተጎድተው ሲወጡ በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ሙጂብ ቃሲም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶታል። በሙከራ ደረጃ 53ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማ ኳስ ሙጅብ ቃሲም በጭንቅላት ገጭቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት ፣ 60ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ወደ ግብ እክርሮ የመታው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ የወጣበት እና 78ኛ ላይ ሙጅብ ቃሲም ከማዕዘን ያተሻማን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ በድጋሜ ኢስማ ያወጣበት በፋሲል ከተማ በኩል የሚጠቀሱ ነበሩ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል  48ኛ ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ሚኬኤል ሳማኪ በቀላሉ ሲያዳነበት 73ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን ሎክዋ ከሳጥን ውጭ የመታው ኳስ ደግሞ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። 

በዚህ መልኩ ጨዋታው ያለምንም ግብ  በአቻ ውጤት ማለቁን ተከትሎ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች 7 ነጥቦችን ሲሰበስቡ ፋሲል ከነማዎች  በአንፃሩ 4 ነጥቦችን በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ 1ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ ፡LINK