በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታ ሶዶ ላይ መቐለ 70 እንደርታን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-0 በማሸነፍ የዓመቱን የመጀመሪያ ሙሉ ሶስት ነጥብ አስመዝግቧል።
በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን በሜዳው ያደረገው ወላይታ ድቻ በሶስተኛ ሳምንት በሀዋሳ በተረታበት ጨዋታ የነበሩትን የአራት ተጫዋቾች በሌሎች ተክቶ ገብቷል። ያሬድ ዳዊት፣ ውብሸት ዓለማየሁ፣ ፍፁም ተፈሪ እና ጸጋዬ አበራ ወደ ተጠባባቂ ወንበር አውርደው ሙባረክ ሽኩር፣ ቸርነት ጉግሳ፣ እዮብ ዓለማየሁ እና አብዱልሰመድ ዓሊን በመጀመርያ አሰላለፍ አካተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል በሁለተኛው ሳምንት ደደቢትን ከረቱበት ስብስብ በዛሬው ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ የነበረውን አማኑኤል ገብረሚካኤል በድንገተኛ ህመም ምክንያት በጋናዊው አጥቂ ማዊሊ አውሲ ተተክቷል። ቀስ በቀስ በበርካታ የድቻ ደጋፊዎች የታጀበው ጨዋታ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ተጀምሯል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከረጃጅም ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን መድረስ ችለዋል። 6ኛው ደቂቃ ላይ ለወላይታ ድቻ ውጤታማነት በመስመር በኩል መልካም አጋጣሚዎችን ሲፈጥር የነበረው ቸርነት ጉግሳ ያሻገረውን ኳስ አንዱዓለም ንገሴ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ብረት ታካ የወጣችው ኳስ ቀዳሚ የጨዋታው ሙከራ ነበረች። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በመቐለ በኩል አማካዩ ጋብርኤል አህመድ ከርቀት አክርሮ የመታት አደገኛ ኳስ ታሪክ ጌትነት አውጥቶበታል። 17ኛው ደቂቃ ላይ አንዱዓለም ንጉሴ ያመቻቸለትን ኳስ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ኄኖክ ኢሳይያስ ከሳጥን ጠርዝ የፊሊፕ ኦቮኖን መውጣት ተመልክቶ በቀጥታ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ነክታ የወጣችበት ሙከራ ምናልባትም ድቻን ቀዳሚ ልታደርግ የተቃረበች አጋጣሚ ነበረች። 22ኛው ደቂቃ ላይ መቐለዎች ምላሽ በመስጠት በግራ የድቻ የግብ ክልል ማዊሊ አሶ ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ ሲመታት በእለቱ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት አውጥቶበታል።
ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ወላይታ ድቻዎች ወደ ቀኝ መስመር አድልተው ሲጫወቱ የታየ ሲሆን በተለይ ቸርነት ጉግሳ በቦታው ላይ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ አመርቂ ነበር። 28ኛ ደቂቃ ቸርነት ወደ መቐለ የግብ ክልል ገብቶ ያመቻቸውን ኳስ አንዱዓለም በቀላሉ አምክኗታል። በተመሳሳይ በመስመር በኩል ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ባደረጉት መቐለዎች በኩልም በ33ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ የፈጠረለትን መልካም የግብ ማግባት አጋጣሚን ያሬድ ቢያገኛትም ዐወል አብደላ እንደምንም አስጣለው እንጂ መልካም አጋጣሚ ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ የሁለቱን ቡድኖች የጨዋታ መንገድ ለመረዳት አዳጋች የነበረ ሲሆን የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት አጋማሽ ነበር። ወላይታ ድቻ እዮብ ዓለማየሁን በፀጋዬ አበራ ተክቶ ካስገባ በኃላ ወደ መቐለ የግብ ክልል በቀላሉ ሲገቡ ታይተዋል። መቐለ ደግሞ ከተከላካይ ከሚላኩ ረጃጅም ኳሶች ያልተሳኩ የማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ አብዱልሰመድ በግንባር ገጭቶ ኢቮኖ የያዘበት እና ጸጋዬ አበራ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የሞከረውና የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣው በድቻ በኩል፤ ማዊሊ ከያሬድ ሀሰን አግኝቶ በቀላሉ ያመከነው ኳስ እና ያሬድ ሀሰን ለማሻማት ጥረት ሲያደርግ አቅጣጫዋን ስታ ታሪክ መረብ ላይ ለማረፍ ስትንደረደር ታሪኬ በአስገራሚ መልኩ ያወጣት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።
82ኛው ደቂቃ ላይ በድቻዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቸርነት ጉግሳ ሁለት የመቐለ ተጫዋቾችን አልፎ የሰጠውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጸጋዬ አበራ በአግባቡ በመጠቀም ወደግብነት ለውጧት ድቻን አሸናፊ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። ከግቧ በኋላም ድቻዎች በመከላከል ውጤታቸውን አስጠብቀው ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ ፡LINK |