የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ስሑል ሽረን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጀመሪያው ሳምንት አስደንጋጭ ሽንፈት ያገገመበትን የ4-0 ድል አስመዝግቧል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ለመገናኛ ብዙሀን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“በዛሬው ድል ማናችንም መወሰድ የለብንም ፤ አሁንም ብዙ ማሻሻል የሚገቡን ነገሮች አሉ፡፡” – ስቲዋርት ሃል
“በዛሬው ድል ማናችንም መወሰድ የለብንም ፤ አሁንም ብዙ ማሻሻል የሚገቡን ነገሮች አሉ፡፡” – ስቲዋርት ሃል
ስለ ጨዋታውና ከቡድኑ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ…
“ጨዋታው ብዙም መጥፎ አልነበረም ፤ አጠቃላይ የቡድኑን የአጨዋወት መንገድ ፎርሚሽኑንም ብቻ ብዙ ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ሞክረናል፡፡ በተጫዋቾቼ በጣም ደስተኛ ነኝ። ላለፉት ሦስት ሳምንታት በጣም ጠንካራ ስራዎችን በልምምድ ላይ ለመስራት ሞክረናል ፤ በዛሬውም ጨዋታ ላይ በልምምድ ላይ በሰራነው መሠረት አቅማቸው የፈቀደውን ለማድረግ ሞክረዋል፡፡”
በቀጣይ መሻሻል ስላለባቸው ነገሮች…
“ሁልጊዜም ለመሻሻል ዕድል ይኖራል፤ ፕሪሚየር ሊጉን በአንድ ጨዋታ ማሸነፍ አይቻልም እኛ ደግሞ የምንጫወተው ሊጎን ለማሸነፍ ነው ስለዚህ በየጨዋታው መሻሻል መቻል አለብን፡፡ በዛሬው ጨዋታ መሻሻል የሚገባቸው የተወሰኑ ድክመቶችን ተመልክቻለሁ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች አጨዋወታችን ፈጣና እና ኃይልን የቀላቀለ ነበር ነገርግን በቀሩት 10 ደቂቃዎች ያንን ማስቀጠል ባለመቻላችን ደከም ብለን ነበር። በዚህም የተነሳ እነሱ የተወሰኑ የማግባት አጋጣሚዎችን ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ይህን ክፍተት መቅረፍ ችለናል፡፡ በዛሬው ድል ማናችንም መወሰድ የለብንም አሁንም ብዙ ማሻሻል የሚገቡን ነገሮች አሉ፡፡”
ስለ ደጋፊው…
“ደጋፊዎቻችን በጣም ጥሩ ናቸው፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ አንዱ ትልቁ ችግር አንዳንድ ጊዜ ደጋፊዎች የተጫዋቾችን ስሜት ይቆጣጠራሉ ይህ ደግሞ ችግር ነው፡፡ ተጫዋች ሁልጊዜም የስሜት መረጋጋት ሊኖረው ይገባል፡፡ ደጋፊዎቻችንን ማክበር ይኖርብናል ፤ ነገርግን መርሳት የሌለብን ነገር ግን ይህንን ስሜት መቆጣጠር መቻል እንዳለብን ነው፡፡ ከዛሬው ጨዋታ በፊት ለተጫዋቾቼ ያልኳቸው ነገር ቢኖር ደጋፊውን መፍራት እንደሌለባቸውና በበጎ ሁኔታ ከተጫወቱ ደጋፊው አብሯቸው እንደሚሆን ነገርያቸው ነበር፡፡”
“አራቱም ጎሎች የተቆጠሩት እኛ በሰራናቸው ስህተቶች ነበር፡፡” – ዳንኤል ፀኃዬ
ስለ ጨዋታው…
“በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጫናዎች ተፈጥረውብን ግብ ላለማስተናገድ በማሰብ ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ጥረት አድርገናል፡፡ እንደተመለከታችሁት አራቱም ጎልች የተቆጠሩት እኛ በሰራናቸው ስህተቶች ነበር፡፡ በተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቻችን ዘንድ ኃላፊነት የጎደለው አጨዋወት ይስተዋል ነበር ፤ ይህም ዋጋ አስከፍሎናል። በተጨማሪም መሀል ሜዳ ላይ የነበሩን ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ተቀይረው ከሜዳ መውጣትና ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾች ጥሩ አለመንቀሳቀስ ጎድቶናል፡፡”
ስለዛሬው የጨዋታ እቅዳቸው…
“የመጀመሪያ ዕቅዳችን የነበረው ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ነበር። ካልሆነም የመጨረሻ እቅዳችን የነበረው አቻ መውጣት ነበር፡፡ ከተጋጣሚያችን ትልቅ ቡድንነት አንፃር ክብር ቢኖረንም በራሳችን ከፍተኛ መተማመን ነበረን ነገር ግን ይህ መተማመን ስህተቶች እንድንሰራ ዳርጎን ልንሸነፍ ችለናል፡፡”