በአራተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ከጨዋታው በኋላ የሰጡትን አስተያየት እነሆ!
“ሙሉ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው
“በጨዋታው በተለይ በመጀመርያ ተሰላፊነትት ባስገባናቸው የአጥቂ መስመር ተጨዋቾቼ ጥሩ አለመሆን እና በተጋጣሚያችን የሰዓት ማባከን ደስተኛ አልነበርኩም። በመጀመሪያው አጋማሽ የአጥቂ መስመር ተጨዋቾቼ ጥሩ ባለመሆናቸው ባላሰብኩት መልኩ ሁለት አጥቂዎችን ቀይሬ አስገብቻለው። ቢሆንም ግን በነበሩት ለውጦች መርካት አልቻልኩም። በጨዋታው ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። ነገር ግን እነዛን አጋጣሚዎች ተጠቅመን ጎሎችን ሳናስቆጥር ነጥብ ተጋርተን ወተናል።”
ስለ ተጨዋቾቻቸው ብቃት
“ተጨዋቾቼ ባሳዩት ነገር ብዙም አልተደሰትኩም። ዛሬ አብዛኞቹ ተጨዋቾቼ ደጋፊውን ለማስደሰት በጣም ጓጉተው ስለገቡ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ነገሮችን ሲያደርጉ አስተውያለው። ስለዚህ በደጋፊያችን ፊት ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘን መውጣት አለመቻላችን ቢያስከፋኝም ዛሬ የነበሩብንን ስህተቶች እንደ ግብዓተትነት ወስደን ለቀጣይ ጨዋታዎች እንዘጋጃለን። ለዛሬው ጨዋታ ሙሉ ሃላፊነቱን እኔ እወስዳለው።”
ስለ ቡድኑ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ እና ስለተጋጣሚያቸው
“በጨዋታው የነበረን ጠንካራ ጎን የተከላካይ መስመራችን ነው። ከኋላ የተሰራው ጥምረት በጣም አስደስቶኛል። ይህንንም ጠንካራ ነገር ደግሞ እናስቀጥላለን። ተጋጣሚያችን ሃዋሳ ከተማዎች ደግሞ በአንድ አጥቂ በመጫወት በሚገኙ ያልታሰቡ እድሎች ጎሎችን ለማስቆጠር ሞክረው የሚፈልጉትን አሳክተው ወጥተዋል።”
“መጀመርያ አቅደን የመጣነው ማሸነፍን ነበር” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ
” በሁለታችንም በኩል የነበረው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነው። እኛም እነሱም በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ነበረ ተከትለን ወደ ሜዳ የገባነው። በሜዳም ላይ የታየው ነገር ይህ ነው። ቡድኔ በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርጓል። ነገር ግን እነዛን ሙከራዎች ወደ ግብነት መቀየር አልቻልንም።”
ስለ ቡድናቸው ከሜዳው ውጪ ስላለበት የውጤት ማጣት
“ዘንድሮ ዋናው አላማችን ከሜዳችን ውጪ፤ በሜዳችን ላይ የሚባለውን ነገር ለማስወገድ ነው። ባለፈውም ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማን ስንገጥም ይሄንኑ አሳይተናል፤ የዳኝነት ችግር ረበሸን እንጂ። ስለዚህ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት መቅረብ ከፈለግን ይህንን ችግር መቅረፍ እንዳለብን ስለተማመንን ይህንን ችግር በፍጥነት እናሻሽላለን።”
ስላገኙት አንድ ነጥብ
“መጀመርያ አቅደን የመጣነው ማሸነፍን ነበር። ለዚህም ማሳያ ደግሞ ከጨዋታው በፊት ባህር ዳርን በፕሪሚየር ሊግ ልምድም በነጥብም እንደምንበልጠው በመነጋገር የማሸነፍ ስነ ልቦና በተጨዋቾቻችን ላይ ገንብተን ለጨዋታው ቀርበናል።በጨዋታውም ደግሞ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎቸን አድርገናል ነገር ግን በነበሩብን የውሳኔ ችግሮች እና የአጨራረስ ስህተቶች ሳናሸንፍ ቀርተናል።”
ስለ ተጋጣሚያቸው
” ባህር ዳር ከተማ በጣም ጥሩ ቡድን ነው። ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት ትላልቅ ቡድኖችን መፈተኑ የሚያስገርም ነው። ዛሬም በጣም ጥሩ ነበር። ነገር ግን እኛ ጥሩ ስለነበርን እና የተከላካይ መስመራችንን ጥሰው መግባት ስላልቻሉ ነው እንጂ ፈትነውን ነበር። ከዛሬው ጨዋታ በፊት ቡድኑ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ተመልክተናል። በነዛም ጨዋታዎች ብቃታቸውን አይተናል። ዛሬ ግን የኛ ጥሩ መሆን ነው እንጂ እነሱም በጥሩ ተንቀሳቅሰዋል።”
ስለ ደጋፊዎች
“ደጋፊዎቹ በጣም የሚገርሙ ናቸው። ትክክለኛ ደጋፊ ማለት ይህ ነው። ምንም ነገር ሳንሆን ነው ጨዋታችንን በነፃነት ያጠናቀቅነው። የደጋፊዎች ጥሩ መሆን ጨዋታው መልኩን እንዳይስት ስላደረገው በደጋፊዎቹ ደስተኞች ነን።”