ሴቶች 2ኛ ዲቪዝዮን | መቐለ የመጀመርያ ድሉን ሲያስመዘግብ ቂርቆስ እና ፋሲል ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ሁለት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተካሂደው መቐለ 70 እንደርታ የመጀመርያ ድሉን ሲያስመዘግብ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል። 

የውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር ላይ ተካተው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንደማይወዳደሩ በመታወቁ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመርሐ ግብሩ ላይ ማስተካከያ አድርጓል። በዛሬው እለትም በሦስተኛ እና አራተኛ ሳምንት ላይ የሚገኙ ሁለት ጨዋታዎች ነው የተከናወኑት። 

08:00 ላይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው የ3ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አካዳሚ ሜዳ ላይ ተከናውኖ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የግብ እድል የፈጠሩት ፋሲሎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። ሐረገወይን ምህረቴ የግቧ ባለቤት ናት። ከእረፍት መልስ ቂርቆስ ክፍለ ከተማዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃ በላይነሽ ልንገርህ የአቻነቱን ጎል አስቆጥራለች። 

የአራተኛው ሳምንት መርሐ ግብር የሆነው የቦሌ ክፍለ ከተማ ጨዋታ 10:00 ላይ በአካዳሚ ሜዳ ተከናውኖ እንግዳው መቐለ 2-0 አሸንፏል። በ18ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በቀጥታ የተሞከረ ኳስ አግዳሚውን ለትሞ ሲመለስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ሳሮን ሠመረ ወደግብነት ቀይራ መቐለን ቀዳሚ ስታደርግ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አማካይዋ ርሻን ብርሀኑ ከተከላካዮች አምልጣ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራለች። ውጤቱን ተከትሎ ዘንድሮ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን ማሳካት ችሏል። 


የሁለተኛ ዲቪዝዮኑ ቀጣይ ጨዋታዎች በዚህ መልኩ የቀን ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል። 

3ኛ ሳምንት
ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2011
ቦሌ ክ/ከተማ 0-2 መቐለ 70 እንደርታ
እሁድ ኅዳር 30 ቀን 2011
ሻሸመኔ ከተማ 09:00 ቂርቆስ ክ/ከተማ
ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2011
አቃቂ ቃሊቲ 09:00 ንፋስ ስልክ ላፍቶ
4ኛ ሳምንት
ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2011
ቂርቆስ ክ/ከተማ 1-1 ፋሲል ከነማ
ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2011
ልደታ ክ/ከተማ 11:00 ቦሌ ክ/ከተማ
ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2011
ሻሸመኔ ከተማ 09:00 አቃቂ ቃሊቲ