ከማል ኢብራሂም፡ ከይርጋጨፌ ሜዳዎች እስከ አውስትራሊያ ኤ ሊግ

ከማል ኢብራሂም በአውስትራሊያ ናሽናል ፕሪምየር ሊግ ቪክቶሪያ (ከአውስትራሊያ ኤ ሊግ ቀጥሎ ያለው ሊግ ነው፡፡) የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል፡፡ ከማል ለፓርት ሜልቦርን ሻርክስ በ28 ጨዋታዎች 10 ግቦችን አስቆጥሮ 8 ግብ የሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡ የ24 ዓመቱ የፓርት ሜልቦርን ሻርክስ የመስመር ተጫዋች ስላሳለፈው የእግርኳስ ህይወት ከሶከር ኢትዮጵያው ኦምና ታደለ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሰኔ 19 1984 በቡና ምርቷ በምትታወቀው ይርጋጨፌ የተወለደው ከማል 5 ወንድሞች እና 2 እህቶች አሉት፡፡ እግርኳስን መጫወት የጀመረው በይርጋጨፌ እያለ ነበር፡፡ ታላቅ ወንድሙ ይርጋጨፌ ለሚገኝ የአካባቢ ቡድን መጫወቱ ከማልን ወደ እግርኳስ እንዲሳብ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡
“የተወለድኩት ይርጋጨፌ ነው፡፡ እናቴ ከዛው ከይርጋጨፌ ስትሆን አባቴ የተወለደው ኤርትራ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ህይወቱን ያሳለፈው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ታላቅ ወንድሜ በይርጋጨፌ ለሚገኝ ቡድን ይጫወት ነበር፡፡ እኔም እሱን እየተመለከትኩ ስላደግኩ እግርኳስን መጫወት ያስደስተኝ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ልጅ እግርኳስ በሰፈር ውስጥ ለደስታ ስል እጫወት ነበር፡፡”
ህይወት ለከማል ቀላል አልነበረችም፡፡ በ1990 የተነሳው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከማልን ከሁለት ወንድሞቹ እና ከአባቱ ጋር አለያየው፡፡ ከማል እና የተቀሩት ቤተሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ መጡ፡፡ ያንን ግዜ ከማል እንዲህ ያስታውሰዋል፡፡
“የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር አባቴ እና ሁለት ወንድሞቼን መንግስት ወደ ኤርትራ ላካቸው፡፡ እኔ ከተቀረው ቤተሰቤ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጣው፡፡ እግርኳስን ሲጫወት የነበረው ታላቅ ወንድሜ ወደ ኤርትራ መሄድ ቢያሳዝነኝም፤ እኔ ግን እግርኳስ መጫወት ቀጠልኩኝ፡፡ ታላቅ ወንድሜ በኤርትራ ለተለያዩ ቡድኖች መጫወት ችሏል፡፡ የኤርትራ ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት መምራት ችሏል፡፡ ለ5 ዓመት በአዲስ አበባ ቆይታዬ የተረዳሁት ነገር በእግርኳስ ስኬታማ መሆን በጣም ከባድ መሆኑን ነበር፡፡ 1996 ላይ ሜልቦርን አውስትራሊያ ይኖር የነበረው አያቴ ሁኔታዎችን አመቻችቶልን ከቤተሰቤ ጋር ወደ እዛው አቀናው፡፡”

 

ለኤርትራ ብሄራዊ ቡድን የተጫወተው የከማል ታላቅ ወንድም
ለኤርትራ ብሄራዊ ቡድን የተጫወተው የከማል ታላቅ ወንድም

በአያቱ አመቻችነት ወደ ሜልቦርን የተጓዘው ከማል በአውስትራሊያ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ለትምህርት ትኩረት መስጠቱን ይናገራል፡፡
“በሜልቦርን አብዛኛውን ግዜዬን በትምህርት ላይ አሳልፍ ነበር፡፡ ሜልቦርን ለኔ አዲስ አከባቢ፣ ባህል እና ህዝብ ያለበት መሆኑ ነገሮችን ለመላመድ ያስቸግር ነበር፡፡ እግርኳስን መጫወት ግን አላቆምኩም ነበር፡፡ በምኖርበት አካባቢ እግርኳስ እጫወት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በሰፈሬ ስጫወት የተመለከተኝ አንድ አውስታራሊያዊ በሱ ስር ወደ ሚተዳደር ቡድን አመጣኝ፡፡ በዛም ቡድን ውስጥ ባሳየሁት ጥሩ እንቅስቃሴ ለክልሌ ቪክቶሪያ ብድን ተመረጥኩኝ፡፡ ህይወት ጥሩ እየሆነች መጣች፡፡ ቪክቶሪያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ስፖርት ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘው፡፡ ይህም ለእግርኳስ ህይወቴ በጣም አስፈላጊ ትምህርትን ያገኘሁበት ቦታ ነበር፡፡”
በቪክቶሪያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ስፖርት ትምህርቱን እየተከታተለ ለአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ተደረገለት፡፡
“ቪክቶሪያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ስፖርት ትምህርቴን እየተከታተልኩኝ ለአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ብድን ጥሪ ተደረገልኝ፡፡ ለ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለሁለት ዓመታት ተጫውቻለው፡፡ በሁለት ዓመት የብሄራዊ ቡድን ቆይታዬ የተለያዩ የዓለም ክፍላትን ማየት ችያለው፡፡ ከብራዚል ጋር ባደረግነው ጨዋታ የኔይማር እና ፊሊፕ ኮቲንሆ ተቃራኒ ሆኜ ተጫውቻለው፡፡ ለ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከ20 በላይ ጨዋታዎች ማድረግ ችያለው፡፡”
ከማል ለአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን መጫወቱ ሌላ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ አስቻለው፡፡
“ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር በነበረኝ ቆይታ ምክንያት ካንቤራ በሚገኘው አውስትራሊያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ስፓርት ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘው፡፡ ኢንስቲትዩቱ አውስትራሊያ ውስጥ አለ የሚባል የስፖርት ማዕከል ነው፡፡ ለመጀመሪያ ግዜም የሜልቦርን ሃርትስ ለተሰኝ የኤ ሊግ ብድን በወጣት ቡድኑ መጫወት ጀመርኩ፡፡”

 

ከማል ኢብራሂም ከአውስታራሊያ ከ19 ዓመት በታች ብሄራዊ ብድን ጋር
ከማል ኢብራሂም ከአውስታራሊያ ከ19 ዓመት በታች ብሄራዊ ብድን ጋር

ሜልቦርን ሃርትስ (በአሁን ግዜ በአቡዳቢው ቱጃር ሼክ መንሱር አል ናህያን ስር እየተዳደረ ሜልቦርን ሲቲ የሚል ስያሜ ተሰጥቶል) ለከማል በ2002 ለመጀመሪያ ግዜ የሶስት ዓመት ውል አቀረበለት፡፡
“ለሜልቦርን ሃርትስ የሶስት ዓመት ውል ፈረምኩኝ፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በኤ ሊግ መጫወት ቻልኩኝ፡፡ ቢሆንም በተደጋጋሚ መጎዳቴ እና በቂ የመሰለፍ ዕድል አለማግኘቶ ክለቡን ሳላገለግል ለቀቁኝ፡፡ በነዚህ አስቸጋሪ ግዜያት የደረሰልኝ ፓርት ሜልቦርን ሻርክስ የተባለ የሁለተኛ ዲቪዚዬን ክለብ ነው፡፡ በፖርት ሜልቦርን ለሶስት ዓመት ተጫውቻለው፡፡ አሁን ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለኔ የተለየ ነበር፡፡ የዓመቱን ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ያገኘሁበት ነበር፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን ከዚህ የተሻለ ነገር ለማድረግ ጠንክሬ እየሰራው ነው፡፡ የተሻለ ነገር ለማሳየት ዕድል ሊሰጥህ ይገባል፡፡ በሜልቦርን ሃርትስ ለኔ ይህንን ዕድል አልሰጡኝም፡፡ ገና ታዳጊ ስለነበርኩ በግዜው በቂ ጥበቃ እና እንክብካቤ አልተደረገልኝም፡፡ አሁንም ከዚህ የተሻለ መስራት እችላለው፡፡ በአውስትራሊያ ለአፍሪካ ተጫዋቾች የሚሰጠው ግምት አነስተኛ ነው፡፡ ይህንን ተቋቁሜ ከተቻለ በአውስትራሊያ አሊያም በአውሮፓ ሊጎች የመጫወት ፍላጎት አለኝ፡፡”

Share2015-10-08-0f975b7014cdae52bab8223f89176f2b1642283f7cdd7220b1e1efad55adaa1a-Picture
እግርኳስ ዓለማቀፋዊ ነው፡፡ ሃገራት ከነሱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ተጫዋቾች ለሃገራቸው ብሄራዊ ቡድን ጠርተው ሲያጫወቱ በሰፊው ይታያል፡፡ አውስትራሊያን ከ17፣ 18 እና 19 በታች ብሄራዊ ቡድን የወከለው እና አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገረው ከማል ዕድሉ ከመጣ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጫወት በሬ ክፍት ነው ይላል፡፡
“ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወት እፈልጋለው፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያ የተሻለ ኑሮ እንድኖር እንዲሁም በእግርኳሱ ህይወቴ ላይ ከአውስትራሊያ በላይ ዕድል ባትሰጠኝም እኔ ግን ፍላጎቴ ለኢትዮጵያ መጫወት ነው፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ጋር መገናኘት ችዬ ነበር፡፡ ፍላጎቴን ተረድቶ ስለኔ አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ ፈልጎ ነበር፡፡ የብሄራዊ ብድኑ ምክትል አሰልጣኝ አድራሻ ስለጠፋብኝ የነበረን ግኙነት ተቋርጧል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ደጋፊ ነኝ፡፡ ለወደፊት ብሄራዊ ብድኑ መልካም ዕድል እንዲገጥመው እመኛለው፡፡”

ያጋሩ