በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን 3ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ መከላከያን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በተመለከትንበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች የግብ እድሎችን በመፍጠሩ ረገድ የተሻሉ ሲሆን መከላከያወች ደግሞ ኳሰን በመቆጣጠሩ ተሽለው ታይተዋል። በ26ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ምርቃት ፈለቀ ያሻማችውን ኳስ ቅድስት ዘለቀ በግንባር ገጭታ ለጥቂት ሲወጣባት 28ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ መሀል ለመሀል በመከላከያ ተከላካዮች አሾልካ የሰጠቻትን ኳስ ነፃነት መና ከግብ ጠባቂዋ ማርታ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝታ አምክናዋለች። መከላከያዎች በአንፃሩ እመቤት አዲሱ ከቅጣት ምት እና ከርቀት ከምትመታቸው ያልተሳኩ ኳሶች ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ የግብ አጋጣሚን መፍጠር ያልቻሉበት ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያዎች በሚገባ ተሻሽለው መቅረብ የቻሉ ሲሆን በመጀመርያ ተሰላፊነት ገብተው የነበሩት መዲና ዐወል እና ሲሳይ ገብረዋህድን አስወጥተው ሄለን እሸቱንየ እና የምስራች ላቀውን ማስገባታቸው ለድላቸው አስተዋፅኦ አበርክቷል። የሀዋሳ ከተማዋ የመሀል ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ በጉዳት መውጣቷ ደግሞ በተከላካይ ክፍሉ ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል።
63ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የሀዋሳ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቃ መከላከያን የተቀላቀለችው መሠሉ አበራ ወደ ግብ ኳሷን ስትልክ የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ አባይነሽ ኤርቄሎ በእጅ ብትይዝም ኳሱ መስመር አልፏል በሚል ፀድቋል። በዚህች ግብ የተነሳ በዳኛዋ ላይ በርካታ ተቃውሞ ከደጋፊዎች ዘንድ ሲነሳም ተስተውሏል። በግቧ የተነቃቁት መከላከያዎች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው ሁለት ደቂቃ ብቻ ነው። 65ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን እሸቱ የሀዋሳ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂን ያለመናበብ ተመልክታ አስቆጥራለች።
ከግቦቹ በኋላ ሀዋሳዎች ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ነፃነት መና በግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ምርቃት ፈለቀ በ78ኛው ደቂቃ ብታስቆጥርም ከጨዋታ ውጭ ተብሎ በመሻሩ ተቃውሟቸውን በመገለፅ በአምበሏ አማካኝነት በዳኛዋ ላይ ክስ ካስያዙ በኃላ ጨወታው ድጋሚ ጀምሯል። በ81ኛው ደቂቃ የሀዋሳ አጥቂ ምርቃት ፈለቀ ከዳኛዋ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባቷ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቷ ቀሪውን ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ሀይቆቹ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀር እታለም አመኑ ከቅጣት ምት ባስቆጠረችው አስደናቂ ጎል ልዩነቱን ቢያጠቡም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በእንግዳው ቡድን መከላከያ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡