በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዛሬ ሀዋሳ ላይ በተደረገ እንድ ጨዋታ ደቡብ ፖሊስን የገጠመው ፋሲል ከነማ በኢዙ ኢዙካ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ በዓመቱ የመጀመርያ የሜዳው ውጪ ሦስት ነጥቡን ሰብስቧል፡፡
የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም በየ15 ቀኑ ሦስት የሊግ ጨዋታዎችን ማስተናገዱን በመቀጠል ዛሬ የደቡብ ፖሊስ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ የተካሄደበት ሲሆን እጅግ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ተመልካች የታደመበት ጨዋታም ነበር። ባለሜዳው ደቡብ ፖሊስ ባለፈው ሳምንት መቐለ ላይ በወልዋሎ ዩዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሽንፈትን ካስተናገደው ቡድን የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ደስታ ጊቻሞን በአዳሙ መሐመድ፣ ዘነበ ከድርን በዮናስ በርታ፣ በረከት ይስሀቅን በልዑል ኃይሌ፣ አዲስዓለም ደበበን በኤርሚያስ በላይ እንዲሁም መስፍን ኪዳኔን በብሩክ ኤልያስ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ አፄዎቹ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለግብ በተለያዩበት ጨዋታ የተጠቀሙትን የመጀመርያ አስራ አንድ ዛሬም ተጠቅመዋል።
በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የሲዳማ የመብት ተሟጋቾችን ለመቀበል ወደ አርሲ ነጌሌ ሲጓዙ በደረሰ የመኪና አደጋ ህይወታቸው ላለፉ አምስት ግለሰቦች የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኃላ የተጀመረው ጨዋታ ከጅማሮው እስከ ፍፃሜው በዝናብ ታጅቦ ተከናውኗል። ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ከሳቢነቱ ይልቅ የሚቆራረጥ የኳስ እንቅስቃሴ የበዛበት ከመሆኑም ባለፈ የቡድኖቹን የአጨዋወት መንገድ በጉልህ ለመረዳት ያላስቻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ተመልክተናል።
10ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ያሻገራትን ኳስ ቤንጃሚን ኤዲ በግንባር ገጭቷት በግቡ አናት በኩል የወጣችበት ኳስ የጨዋታው ቀዳሚ ለግብ የቀረበ ሙከራ ስትሆን 14ኛው ደቂቃ ፖሊሶች በመልሶ ማጥቃት ምላሽ ለመስጠት በፈጠሩት አጋጣሚ ልዑል ኃይሌ ያገኛትን ኳስ በቀላሉ አምክኗታል። በቀሪው የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች የመስመር አጥቂዎቻቸውን በመጠቀም የጎል እድል ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ስኬታማ አልነበረም። 18ኛው ደቂቃ ሰዒድ ሁሴን በቀኝ በኩል ከሽመክት ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ከገቡ በኋላ ኤፍሬም ዓለሙ የሞከረውና ግብ ጠባቂው ፍሬው የያዘበት በአፄዎቹ በኩል፤ በ45ኛው ደቂቃ አበባው ቡጣቆ ከግራ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻማውን ብሩክ ኤልያስ በቀላሉ ካመከናት ኳስ ውጪም በዚህ አጋማሽ የጠሩ የጎል አጋጣሚዎችን ሳንመለከት ቀርተናል።
ከእረፍት መልስ አፄዎቹ የተጫዋች ለውጥ ስኬታማ ሲያደርጋቸው ደቡብ ፖሊሶች በተቃራኒው ሙሉዓለም ረጋሳን ቀይረው ካስወጡ በኃላ በመሀል ሜዳ ላይ የተቀዛቀዙበት ነበር። 50ኛው ደቂቃ ብሩክ ኤልያስ ያመቻቸለትን ኳስ መስፍን በቀላሉ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ሙከራም በዚህ አጋማሽ ሊጠቀስ የሚችል ብቸኛ የጎል አጋጣሚ ነበር።
በዛብህ መለዮ እና ናይጄሪያዊው አጥቂ ኢዙ ኢዙካን ቀይረው ካስገቡ በኋላ አጼዎቹ የተሻለ ብልጫ በማሳየት ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን 66ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ አክርሮ መትቶ አግዳሚውን ታኮ ሲወጣበት በ82ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አምሳሉ ጥላሁን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ናይጄርያዊው አጥቂ ኢዙ ኢዙካ በግንባሩ በመግጨት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ በፋሲል ከነማ 1-0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ፌዴራል ዳኛ በፀጋው ሽብሩ ጨዋታውን በተረጋጋ ሁኔታ በመምራት ለሶስት የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ አሳይተዋል።
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ፡ LINK |