ከዕለተ አርብ ጀምሮ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እየተከናወኑበት ያለው የሀዋሳ ስታድየም ዛሬም በሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ መካከል የተደረገውን ጨዋታ አስተናግዶ ሀይቆቹ የ2-0 ድል ቀንቷቸዋል።
የባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ እና ከአዳማ ተጉዘው የመጡ በርካታ ደጋፊዎች በታደሙበት የዕለቱ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ባህርዳር አቅንተው ያለ ግብ ካጠናቀቁበት ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች መካከል የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ነው የገቡት። በለውጦቹም ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆን እና አክሊሉ ተፈራን በሶሆሆ ሜንሳ እና ገብረመስቀል ዱባለ ተክተዋል። አዳማ ከተማዎች ደግሞ በአራተኛ ሳምንት ከሲዳማ ጋር አንድ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ ሱራፌል ዳንኤልን በዳዋ ሆቴሳ ብቻ ነበር የለወጡት።
ትናንት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የሲዳማ የመብት ተሟጋቾችን ለመቀበል ሲጓዙ በደረሰ አደጋ ህይወታቸው ላለፉ ግለሰቦች ለማሰብ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኃላ ነበር ጨዋታው ከተያዘለት ሰዓት በ11 ደቂቃዎች ዘግየት ብሎ የጀመረው።
የጨዋታው ሙሉ ደቂቃዎች የሀዋሳ ከተማ የእንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ የበላይነት የታየባቸው እና የአዳማ ከተማ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተስተዋለባቸው ነበሩ። ሀዋሳዎች በተለይ የመጀመሪያወቹን 20 ደቂቃዎች የበላይነታቸው ከፍ ብሎ የታየ ሲሆን በተለይም የዳንኤል ደርቤ እና ደስታ ዮሀንስ የመስመር እንዲሁም የኄኖክ ድልቢ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ጥንካሬን አላብሷቸዋል። አዳማዎች ግን በቀኝ መስመር በረከት ደስታ ከሚያደርገው የግል እንቅስቃሴ ውጪ እምብዛም ተፅዕኖ ማሳደር አልቻሉም።
በሙከራ ደረጃ ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ሀዋሳ ከተማዎች የአዳማን የግብ በር መፈተሽ የጀመሩት። በሙከራው ኄኖክ ድልቢ በቀኝ በኩል ወደ ግብ የላካትን ኳስ ደስታ ዮሀንስ ገጭቶ በግቡ ቋሚ ስር አልፋበታለች። በረከት ደስታ በግል ጥረቱ ሁለት ጊዜ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ዘልቆ ገብቶ ሶሆሆ ሜንሳ የያዘበት አዳማዎች ያደረጓቸው ሁለት ሙከራዎች ነበሩ። ሀዋሳዎች በመስመር የፈጠሩት ተደጋጋሚ ጥቃት 25ኛው ደቂቃ ላይ ሰምሮላቸዋል በቀኝ የአዳማ የግብ ክልል ላይ ዳንኤል ደርቤ በቀጥታ ወደ ግብ ያሻገረውን በቁመት አጭሩ አማካይ ታፈሰ ሰለሞን ተስፋዬ በቀለ እና ቴዎድሮስ በቀለ ባሉበት መሀል ያገኛትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ በኃላ አምበሉ ዳንኤል ደርቤ በጉዳት ሲወጣ የሀዋሳዎች ቀኝ መስመር የተወሰነ መቀዛቀዝ አሳይቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም የባለሜዳው ኃያልነት የታየ ቢሆንም አዳማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ስህተታቸው በመጠኑም ቢሆን ቀርፈው ለመግባት ሞክረዋል። ይሁንና ሀዋሳ ከተማዎች የበላይነታቸው ቀጥሎ ታይቷል። በዚህም 52ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሃንስ ከቅጣት ምት ያሻማት እና አዲስአለም ተስፋዬ ለጥቂት ያመለጠችው ኳስ ተጠቃሽ ስትሆን ገብረመስቀል ዱባለ በተደጋጋሚ ወደ ግብ ክልል እየገባ በቀላሉ የሚያመክናቸው ኳሶችም ለቡድኑ የሚያስቆጩ ነበሩ። በተቃራኒው 60ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ኢስማኤል ሳንጋሬ የሰጠውን ኳስ አዲስ ህንፃ አክርሮ መቶ በግቡ የላይኛው ብረት ተጨርፋ የወጣችበት ኳስ ደግሞ አዳማን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። ሙከራዋ የአዳማዎች የጨዋታው ጠንካራ የምትባል ብቸኛ ሙከራም ነበረች።
ሆኖም 66ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በግራ በኩል ገብረመስቀል ዱባለ እየገፋ ወደ ሳጥን ያስገባውን ኳስ በመቀበል በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ሰጥቶት እስራኤል በሮበርት ኦዶንካራ መረብ ላይ አሳርፎ የሀይቆቹን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ በኃላ አዳማዎች አንድም የግብ ሙከራን ሳያደርጉ ሀዋሳ ከተማዎች በአንፃሩ በእስራኤል እሸቱ አማካይነት ሁለት ጊዜ ግልፅ አጋጣሚን ፈጥረው ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሀዋሳ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ የዳኙበትን ይህን ጨዋታ በተረጋጋ የውሳኔ አሰጣጥ በብቃት መርተውታል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከአዳማ ከተማ ተጉዘው የመጡት በርካታ ደጋፊዎች የአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም እና የስራ አስኪጁን አቶ አንበሴን ስም እየጠሩ ከፍተኛ ተቃውሟቸውን የገለፁ ሲሆን በተቃውሞው የተነሳ የአዳማ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ለ16 ደቂቃዎች ከሜዳ ሳይወጡ በቆዩበት ክስተት የዕለቱ የስታዲየም ውሎ ተደምድሟል።
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ: LINK |