በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ሐረር ላይ ድሬዳዋ ከተማ ደደቢትን 2-0 ሲረታ ስሑል ሽረ ጅማ አባ ጅፋርን አስተናግዶ በሜዳው ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ያለግብ አቻ ተለያይቷል።
ስሑል ሽረ 0-0 ጅማ አባ ጅፋር
ሽረ ላይ ጅማ አባጅፋርን ያስተናገደው ስሑል ሽረ ለተከታታይ ሶስተኛ ጊዜ አሁንም በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ሳይችል ቀርቷል። በውጤቱም ከሊጉ ቻምፒዮን አባ ጅፋር ጋር ያለ ግብ ጨዋታውን አጠናቋል።
የመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች መካከል ፈጣን የማጥቃት እንቅሳቃሴ የተስተዋለ ሲሆን በአስረኛው ደቂቃ ላይም ከመሃል ሜዳ የተሻማውን ረጅም ኳስ ሰይድ ሁሴን በማግኘት በግንባሩ ወደ ግብ ቢሞክርም የጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄይ በቀላሉ ሊያድንበት ችሏል። በመልስ ምት በቀጠለው ጨዋታ በ12ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ መስዑድ መሀመድ መሬት ለመሬት የላካትን ኳስ ዲዲዬ ለብሪ ወደ ፊት በመግፋት ብቻውን ከግብ ጠባቂው ሮቲና ጋር ቢገናኝም ተረጋግቶ ለመምታት ሲሞክር የስሑል ሽረ ተከላካዮች ደርሰው አስጥለውታል። ይህም ለጅማ አባ ጅፋር የሚያስቆጭ የግብ አጋጣሚ ነበር። በጥሩ የመጫወት መንፈስ ላይ በነበሩት ስሑል ሽረዎች በኩል በ17ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ሰይድ ሁሴን አግኝቶ ወደ ግብ በግንባሩ ቢሞክርም ከአግዳሚው በላይ ለጥቂት ሊወጣ ችሏል።
በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበረው የአባ ጅፋሩ ዲዲዬ ለብሪ ከማዕዘን ምት መምቻ አካባቢ ከመስዑድ ጋር በጥሩ ቅብብል በማድረግ ያገኘውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው ሰንደይ ሮቲና ሊያድንበት ችሏል። ግብ ለማግኘት ተጭነው በመጫወት በተደጋጋሚ ወደ ጅማ ግብ ክልል የደረሱት ስሑል ሽረዎች በ34ኛው ደቂቃ ሚድ ፎፎና ከጅላሎ ሻፊ የተሻገረለትን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታም የጅማ አባ ጅፋር ግብ ጠባቂ በጥሩ ብቃት ሊያድንበት ችሏል። የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ እና ግብ ለማግባት ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ማጥቃት የጀመሩት የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በ37ኛው ደቂቃ ላይ የስሑል ሽረ ተከላካዮች በፈጠሩት ስህተት የተገኘውን ኳስ መስዑድ መሀመድ ደርሶ ወደ ግብ ሞክሮ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት የቡድኑ የሚያስቆጭ ሙከራ ነበር። በመልሶ ማጥቃት በቀጠለው ጨዋታ ከደሳለኝ ደባሽ የተሻማውን ኳስ ፎፎና አግኝቶት ሁለት የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በጥሩ ሁኔታ አልፎ ቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርም አጄዬ አድኖበታል።
ከዕረፍት መልስ አካላዊ ንክኪ እንዲሁም የተጫዋቾች ያልተገባ ባህሪ የበዛበት ጨዋታ የተስተዋለ ሲሆን ከመጀመርያው ምዕራፍ ቀዝቀዝ ያለ እና በሁለቱም ቡድኖች የጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ተስተውሏል። ጨዋታው እምብዛም የግብ ሙከራ እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ያለምንም ግብ ተጠናቋል፡፡
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ: LINK |
ድሬዳዋ ከተማ 2-0 ደደቢት
የድሬዳዋ ስታድየም በዕድሳት ላይ በመሆኑ ምክንያት ጨዋታው ከ2006 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በሐረር ስታድየም በተካሄደው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 2-0 አሸናፊ ሆኗል። ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ከተረታ ከ42 ቀናት በኋላ የሊግ ጨዋታ ያደረገ ሲሆን ደደቢቶች ደግሞ ስምንት ቀናት ልምምድ ካቆሙ በኃላ ከፋይናንስ ችግሮች ጋር እየታገሉ ነበር የዛሬውን ጨዋታ ያደረጉት።
በጨዋታው ደደቢቶች ሽንፈት ይግጠማቸው እንጂ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን ድሬዎች ደግሞ በረጃጅም ኳሶች ለመጠቀም ያለመ እንቅስቃሴን ያሳዩበት ነበር። ይሁንና ባለሜዳዎቹ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ የተሻሉ ነበሩ። 27ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ከዘነበ ከበደ የተሻገረችን ኳስ ላይቤሪያዊው አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኒ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢት ተከላካዮች በግብ አስቆጣሪው ኢታሙና ኬይሙኒ ላይ በሳጥን ውስጥ በሰሩት ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት በፍቃዱ ደነቀ አማካይነት አስቆጥረው 2-0 ማሸነፍ ሲችሉ ደደቢት አራተኛ ተከታታይ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
ዮሀንስ ሳህሌ – ድሬዳዋ ከተማ
” ከ42 ቀናት በኃላ ነው ዛሬ በሜዳችን ጨዋታ ያደረግንው። አስቀድመን ደደቢቶች እንደሚከብዱን ገምተን ነበር። ነገር ግን ጨዋታው ተመጣጣኝ ቢሆንም ሁለት ግቦችን አስቆጥረን ወጥተናል የበላይነትን እንደማሳየታችን ደግሞ ውጤቱም ይገባናል”
ኤልያስ ኢብራሂም – ደደቢት
“ድሬዳዋም እኛም ጥሩ ነበርን። በሁለተኛው አጋማሽ ላይ እኛም ጥሩ ነበርን ። የጎል ዕድሎችን ፈጥረን መጠቀም ባለመቻላችን ዋጋ ከፍለናል። ዳኞች የሚወስኗቸው ውሳኔወችም ተገቢ አልነበሩም። ለዚህ ማሳያ የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ተገቢ አልነበረም። ሁለታችንም ጥሩ የነበርን ቢሆንም ለኔ ውጤቱ አላሳመነኝም”
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ: LINK |