በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ሁለተኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ጅማ አባ ቡና እና ቤንቼ ማጂ ቡና ድል ቀንቷቸዋል።
ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡና ከንባታ ሺንሺቾን አስተናግዶ 3-1 በማሸነፍ ዓመቱን በድል ጀምሯል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ሳምንት ከቢሸፍቱ አውቶሞቲቭ እና ከአርባምንጭ ከተማ ሊያደርጉት የነበሩት ጨዋታዎች ወደ ሌላጊዜ በመዘዋወሩ የዛሬው ጨዋታ የመጀመርያቸው ነበር፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ እና ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት በሁለቱም ቡድኖች የተስተዋለ ሲሆን 5ኛው ደቂቃ የአባቡና ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ብርሃኑ አርዴሎ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ በሺንሺቾ በኩል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
በ13ኛው ደቂቃ አባቡና ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በሺንሺቾ ተከላካዮች ርብርብ ግብ ለመሆን ሳይችል ሲቀር የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን በመጠቀም በ20ኛው ደቂቃ ብርሃኑ አርዴላ ከግራ መስመር ያሻገረውን አገኘሁ ተፈራ በማስቆጠር ሺንሺቾዎችን ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም መሪነታቸው እብዛም አልቆየም። 21ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው አክርሮ በመምታት ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከእረፍት መልስ ጅማ አባ ቡናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ተነቃቅተውና አጥቅተው በመጫወት ጫና በመፍጠር በ47ኛው ደቂቃ በእለቱ ጥሩ ሲቀሳቀስ የነበረው ካሚል ረሺድ አክርሮ የመታውን ግብጠባቂው በአግባቡ ኳሱን ባለመያዙ በቅርብ የነበረው ፉዐድ ተማም ባስቆጠረው ጎል መሪ መሆን ችለዋል። በ50ኛው ደቂቃ ደግሞ ከግራ መስመር ዳንኤል ራመቶ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በቀጥታ መረብ ላይ በማሰፍ ባለሜዳዎቹን አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሯል። በእለቱ ለተቆጠሩት ግቦች ከሰዓት አጠባበቅና ከቦታ አያያዝ በተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ የነበረው የሺንሺቾ ግብ ጠባቂ ተሾመ ታደሰ በ57 ደቂቃ ተቀይሮ ወጥቷል ፡፡
ሚዛን አማን ላይ ሀድያ ሆሳዕናን ያስተናገደው ቤንጂ ማጂ ቡና 2-0 ማሸነፍ ችሏል። ቤንች ማጂዎች ተጋጣሚያቸውን ከተማ ከመግባታቸው በፊት ከ20 ኪ.ሜ ቀደም ብለው በማጀብ የተቀበሉ ቢሆንም በዚህ ወቅት ባለው ዝናባማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ምቹ ሜዳ እንዳልገጠማቸው ሆሳዕናዎች ገልፀዋል። የቤንች ማጂን ጎሎች ያስቆጠሩት ወንድማገኝ ኬራ እና ከማል አቶ ናቸው። ከታሰበው ሰአት ቀደም ብሎ በ 7:00 ሰዓት የተጀመረው የሻሸመኔ ከተማ እና የነገሌ ቦረና እንዲሁም ከፋ ቡና ከአርባምንጭ በተመሳሳይ አንድ አቻ ተጠናቀዋል።