ሪፖርት | ወልዋሎ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር አዲስአበባ ስታዲየም ላይ መከላከያን የገጠመው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በአፈወርቅ ኃይሉ ብቸኛ ግብ 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። 

መከላከያ በሳምንቱ አጋማሽ በሬንጀርስ ኢንተርናሽናል ሽንፈት ካስተናገደው የቡድን ስብስብ ውስጥ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔን በአቤል ማሞ በተከላካይ መስመር አዲስ ተስፋዬን በምንተስኖት ከበደ እንዲሁም አማካይ ስፍራ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስን በዳዊት ማሞ ተክቶ ጨዋታውን ጀምሯል፡፡ በተቃራኒው እንግዳዎቹ ወልዋሎዎች ባሳለፍነው ሳምንት ደቡብ ፖሊስን ከረታው ቡድን ውስጥ ምንም አይነት ቅያሪ ሳያደረጉ ነበር በተመሳሳይ የቡድን ስብስብ ጨዋታውን የጀመሩት፡፡

እጅግ ቀዝቃዛና በስታዲየሙ ለታደመው የስፓርት ቤተሰቡ አሰልቺ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ አልነበረም፡፡ መከላከያዎች በተወሰነ መልኩ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢኖራቸውም የወልዋሎን ተከላካዮችን አልፈው የጠራ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡

መከላከያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጓቸው በንጽጽር የተሻሉ የሚባሉት ሙከራዎች በሁለት አጋጣሚዎች ምንይሉ ወንድሙ እንዲሁም ሳሙኤል ታዬ በአንድ አጋጣሚ በቀጥታ ከሳጥን ውጪ የተሞከሩና ኢላማቸውን ያልጠበቁ ኳሶች ነበሩ፡፡ በአንጻሩ በቀጥተኛ አጨዋወት ፊት ላይ በተሰለፈው ሪችሞንድ አዶንጎን የመጀመሪያ ኳስ የማሸነፍ የበላይነትና በፈጣኖቹ ኤፍሬም አሻሞና ፊሲይኒ ፍጥነት ላይ ያተኮሩ በሚመስል መልኩ በርካታ ረጃጅም ኳሶችን ሲጥሉ ቢስተዋልም ውጤታማ ግን አልነበሩም፡፡ ኤፍሬም አሻሞ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል በግሉ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢችልም እንደ ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ደካማ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ መከላካያዎች ዳዊት ማሞን አስወጥተው ዳዊት እስጢፋኖስን በማስገባት በመጀመሪያ አጋማሽ ይታይባቸው የነበረውን የፈጠራ ችግር ለመቅረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በአንጻሩ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ወልዋሎዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በሁለተኛው አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አስፈሪ ነበሩ፡፡

በ57ኛው ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ አዶንጎ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ የመታው ኳስ በመከላከያ ተጫዋቾች ተደርቦ ሲመለስ ኤፍሬም አሻም በድጋሚ ወደ ግብ የላካትን ኳስ አቤል ማሞ ያዳነበት እንዲሁም በተመሳሳይ በ61ኛው ደቂቃ አዶንጎ አግኝቶ ሳይጠቅመበት የቀሩት ኳሶች ተጠቃሽ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ነበሩ። መከላከያዎች በበኩላቸው የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 63 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል። በዚህም ምንይሉ ወንድሙ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት እስጢፋኖስ ቢሞክርም የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ኬይታ በቀላሉ አድኖበታል፡፡

በ67ኛው ደቂቃ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዋለልኝ ገብሬን ከፍሬው ሰለሞን ጋር ተላትሞ ባስተናገደው ከፍተኛ ጉዳት ያጡት ወልዋሎዎች በመጨረሻው አስር ደቂቃ የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አግኝተዋል። በ80ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ አማካዩ አፈወርቅ ኃይሉ ከራሳቸው ሜዳ በአስደናቂ ፍጥነት ያስጀመረውን ኳስ ከሪችሞንድ ጋር በጥሩ መልኩ ተቀባብሎ ካለፈ በኃላ ድንቅ ግብን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ወልዋሎዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ይበልጥ በጥንቃቄ ሲጫወቱ በአንጻሩ መከላከያዎች በተቻላቸው አቅም የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በተጨማሪ ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች ማለትም መከላከያዎች በፍሬው ሰለሞን እንዲሁም ወልዋሎዎች በአማኑኤል ጎበና አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡

በውጤቱ መሠረት የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኗቸው የነበሩት ወልዋሎዎች ለተከታታይ ሁለተኛ ሳምንት ድል በማድረግ በማንሰራራት ችለዋል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ | LINK