በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ከሜዳው ውጭ መከላከያን 1-0 ማሸነፍ ችሏል። ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“በጨዋታው ተጫዋቾቼ ላሳዩት መነሳሳት ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡”- ጸጋዬ ኪዳነማርያም (ወልዋሎ)
ስለ ጨዋታው
“ሊጉ ከተጀመረ ዛሬ አራተኛ ጨዋታችንን አድርገናል። አጀማመራችን ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም፤ በሂደት የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም ጥሩ መሻሻሎች እያሳየን መጥተናል፡፡ ተጋጣሚያችን መከላከያ አብሮ የቆየ ቡድን ነው። በተጨማሪም በቴክኒኩ ረገድ ቀላል የሚባል ቡድን አይደለም። እኛ ደግሞ ከሜዳ ውጪ እንደመጫወታችን ጥንቃቄን መርጠን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረናል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል። ነገርግን ካስቆጠርነው ግብ ይልቅ ብዙ እድሎችን አሞክነናል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ተጫዋቾቼ ላሳዩት መነሳሳት ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡”
“አሁንም በአጥቂዎቻችን መካከል የመናበብ ችግር አለ፡፡”- ሥዩም ከበደ (መከላከያ)
ስለ ጨዋታው
“በመጀመሪያው አጋማሽ ከሞላ ጎደል ጥሩ አልነበረንም። በሁለተኛው አጋማሽ ቅያሬዎችን አድርገን የተሻለ ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ራሳችን በሰራናት አንድ ስህተት ግብ ብናስተናግድም በሁለተኛው አጋማሽ እንደ ቡድን የተሻለ ተንቀሳቅሰናል፡፡”
ስለተደረጉት የተጫዋቾች ለውጦች
“በዛሬው ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ቡድናችን ውስጥ የተሻለ የፈጠራ ብቃት ያለውን ዳዊት እስጢፋኖስን አስቀምጠን በሌሎች ተጫዋቾች ለመጠቀም አቅደን ገብተን ነበር። በተመሳሳይ አጥቂ መስመር ላይ በከፍተኛ ሊግ ጥሩ ልምድ ያለውን ፍቃዱ ዓለሙን ለመጠቀም ሞክረናል። በሁለተኛው አጋማሽ ዳዊት ቀይረን ካስገባነው በኃላ የተሻለ ለማስከፈት የሚችለውን ሞክሯል፤ ነገርግን አሁንም በአጥቂዎቻችን መካከል የመናበብ ችግር አለ፡፡”