የ2011 የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ሽረ ላይ በተደረገ ጨዋታ ሲጀምር ስሑል ሽረ ሲዳማ ቡናን አሸንፏል። ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 2-2 በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት ሽረ 3-1 አሸንፎ ነው ወደ ሩብ ፍፃሜው ያመራው።
ቀዝቀዝ ባለ የአየር ሁኔታ እና በመጠነኛ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ እንግዳዎቹ ሲዳማዎች ተጭነው በመጫወት በተደጋጋሚ ወደ ስሑል ሽረ የግብ ክልል በመድረስ አስደንጋጭ የሚባሉ በርካታ አጋጣሚዎችን በሙሉ ደቂቃው በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ስሑል ሽረዎች በ25ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ጎሏ ሚድ ፎፎና ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ሲተፋት ገና በሁለተኛው ደቂቃ ሰይድ ሁሴን በጉዳት በመውጣቱ ተክቶት የገባው ልደቱ ለማ ደርሶ ያስቆጠራት ነበረች።
ከዕረፍት መልስ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ተጫውተዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው አዲስ ግደይ በ59ኛው ደቂቃ ከሐብታሙ ገዛኸኝ ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት ለውጧት አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሲዳማ ቡና ግብ ክልል የደረሱት የስሑል ሽረ ተጫዋቾች በማዕዘን ምት በኩል ክብሮም ብርሀነ በ78ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ለማሻማት የመታት ኳስ ወደ ግብነት ተቀይራ ባለሜዳዎቹ ዳግም መምራት ጀምረዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ልማደኛው አዲስ ግደይ የሽረው ግብ ጠባቂ ሰንደይ ሮቲሚ ቦታውን ለቆ መውጣቱን ተመልክቶ ከመስመር የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠሩ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2 ለ 2 ተጠናቋል።
ወደ ቀጣይ ዙር የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ስሑል ሽረ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አላፊ ሆኗል። በመለያ ምቱ በሽረ በኩል ኪዳኔ አሰፋ ፣ ሚድ ፎፋና እና ልደቱ ለማ ሲያስቆጥሩ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ሰንደይ ሙቱኩ ፣ ግሩም አሰፋ እና ሚሊዮን ሰለሞን አምክነዋል።
ስሑል ሽረ በቀጣዩ ዙር የኢትዮጵያ ቡና እና የደደቢትን አሸናፊ የሚገጥም ይሆናል።
ቀጣይ ጨዋታዎች
ታህሳስ 24
ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ፋሲል ከነማ
ታህሳስ 30
መከላከያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ወደ ፊት ቀናቸው የሚገለፁ
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባ ጅፋር
አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ
መቐለ 70 እ. ከ ደቡብ ፖሊስ
ኢትዮጵያ ቡና ከ ደደቢት