ካለፉት ዓመታት አንፃር የተቀዛቀዘ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የ2018/19 የውድድር ዘመን የመጀመርያውን ጎሉን አስቆጥሯል።
በ17ኛ ሳምንት ትላንት ማምሻውን በአሌክሳድርያ ስሞሃ በሜዳው ከቀድሞው የኡመድ ክለብ አል ኢትሀድ ጋር ያደረገው ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል ማግኘት የተሳናቸው ባለሜዳዎቹ ስሞሀዎች ከእረፍት መልሰ ነበር በ54ኛው ደቂቃ በኡመድ ኡኩሪ ጎል ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ይህችም ጎል ለኡመድ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ጎል ሆና ተመዝግባለች። ኡመድ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን ቡድኑ ሦስት ነጥብ ይዞ ይወጣል ተብሎ ሲጠበቅ አይቮሪኮስታዊው ራዛቅ ሲሴ ለኢትሀድ በጭማሪ ደቂቃ 90+6 ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ስሞሀም በ21 ነጥቦች በስድስተኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።
በስሞሃ ሁለተኛ ዓመቱን እያስቆጠረ የሚገኘው ኡመድ በዘንድሮ ዓመት በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ በመጀመርያ ተሳላፊነት እየተጫወተ ቢገኝም በሚጠበቀው ደረጃ ጎል ለማስቆጠር ተቸግሮ ቆይቷል። ሆኖም ትላንት የውድድር ዓመቱን የመጀመርያውን ጎል ማስቆጠሩ ለቀጣይ ጨዋታዎች ያነቃቀዋል ተብሎ ይገመታል።
ኡመድ በ2016 ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ አምርቶ 11ጎሎች በማስቆጠር በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ ጎሎችን ያስቆጠረ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ሲታወቅ ከወዲሁ 7 ጎሎች ላይ የደረሰው ሽመልስ በቀለ ዘንድሮ ካልሰበረበት በቀር ይህን ታሪክ ይዞ የሚቀጥል ይሆናል።
በዚሁ የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ሰኞ እለት ሽመልስ በቀለ በአምበልነት የሚመራው ፔትሮጄት በአል ሞካውሉን 3-0 ተሸንፎ በወራጅ ቀጠናው ለመቆየት ሲገደድ ጋቶች ፓኖም የሚገኝበት ኤል ጎውና ከኢስሜይሊ ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ በአፍሪካ ውድድር ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።