ጅማ አባ ጅፋር በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የአንደኛ ዙር ጨዋታው የግብፁን አል ኢህሊን ለመግጠም18 ተጫዋቾችን በመያዝ ትላንት እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ካይሮ ይጓዛል ተብሎ ቢጠበቅም አስቀድሞ ትኬት ባለመቆረጡ ምክንያት ሳይጓዝ ቀርቷል።
ከክለቡ ሰዎች እየተነገረ እንዳለው ከሆነ ለጉዞው መስተጓጎል እንደ ምክንያት የቀረበው አስቀድሞ ቡክ ቢደረግም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሄድ ሲደርሱ ሲስተም ላይ እንዳልተሞላና አውሮፕላኖች በሙሉ መያዛቸው ተገልጾላቸው እንዳልተጓዙ ሲገለፅ ከዚህ ጉዳይ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ጠይቀን እንደተረዳነው ከሆነ ደግሞ ችግሩ የተፈጠረው የቪዛው ጉዳይ አስቀድሞ ያለቀ ቢሆንም ትኬት ሳይቆርጡ ቆይተው ለዛሬ ጉዞ ዛሬውኑ ትኬት በመቁረጥ ለመጓዝ በመፈለጋቸው ጉዞው ሳይሳካ መቅረቱን ለማረጋገጥ ችለናል።
ጅማ አባጅፋር ምንም እንኳ በአፍሪካ ውድድሮች የመጀመርያው ተሳትፎ ቢሆንም በርከት ያሉ ውስብስብ ችግሮች በክለቡ ውስጥ እንዳሉ እየተነገረ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት በእንደነዚህ ባሉ ከፍ ያሉ ውድድሮች ተሳታፊ መሆኑ እየታወቀ እና ስራዎችን በሚገባ ተቆጣጥሮ መስራት እየተቻለ ለዛሬ ጉዞ ዛሬ ትኬት ለመቁረጥ ማሰቡ በጣም አስገራሚ ሆኗል። ለዚህም ለተፈጠረው ችግር ኋላፊነቱን የሚወስደው አካልስ ማነው? የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያሻው ሆኗል።
አባጅፋር የትናንቱ ጉዞ መስተጓጎሉን ተከትሎ ዛሬ ልምምዱን እዚሁ አዲስ አበባ በመስራት እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ግብፅ እንደሚያቀና ይጠበቃል። ጨዋታው ነገ ምሽት 2:00 ላይ ይከናወናል።