የናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ የግብፅ ሊግ ያልተሳካ ቆይታ ተጠናቋል።
አምና ሳይጠበቅ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒየን በሆነው ጅማ አባጅፋር ውስጥ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት በ23 ግቦች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው እና ከክለቡ ጋር ቀሪ ውል እያለው በተጭበረበረ ሰነድ የግብጹን ኢስማይሊ የተቀላቀለው ኦኪኪ አፎላቢ ከአዲሱ ክለቡ ጋር ከአምስት ወራት ያልተሳካ ቆይታ በኃላ መለያየቱን የግብፁ ድረ ገፅ ኪንግ ፉት ዘግቧል።
ከመጀመሪያው በውዝግቦች ታጅቦ ግብፅ የደረሰው ናይጄሪያዊዉ አጥቂው በክለቡ በነበረው የአምስት ወራት ቆይታ በአጠቃላይ ለስድስት ያህል ጨዋታዎች ብቻ ተሰልፎ መጫወት ችሏል ፤ ከነዚህም ውስጥ በሊጉ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያደረገው፡፡ ክለቡ ኢስማይሊ ትናንት ማምሻውን በአረብ ሊግ በሞሮኮው ራጃ አትሌቲክ ክለብ በመለያ ምት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑን ተከትሎም ከተጫዋቹ ጋር መለያየቱ ተሰምቷል፡፡
ከተጫዋቹ በተጨማሪ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት የፖርቹጋል እና የብራዚል ጥምር ዜግነት ያላቸው እንዲሁም ከዚህ ቀደም ሌላኛውን የሊጉ ተሳታፊ ስሞሀን እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢትሃድ ከልባን ጨምሮ ሌሎች ክለቦችን ያሰለጠኑት የ65 ዓመቱ የጆርቫን ቬየራም ከትላንቱ ሽንፈት በኃላ በተመሳሳይ ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየታቸው ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግብፅ ሊግ 13 ጨዋታዎችን አድርገው በ13 ነጥብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት ኢስማይሊዎች በመጪው ቅዳሜ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አንደኛ ዙር ከካሜሮኑ ኮተን ስፓርት ይጫወታሉ፡፡