ኢትዮጵያ 3-0 ሳኦቶሜ – የጨዋታው ምልከታ

በዮናታን ሙሉጌታ


 

በ2018 በሩሲያ ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ አቻውን በደርሶ መልስ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ማጣሪያ አልፏል፡፡ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከትላንት በስተያ በተደረገውና ብሔራዊ ቡድናችን 3-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ምንም እንኳን በቅርብ ከተደረጉ ጨዋታዎች በጥራት ያነሰ ቡድንን ያገኘ ቢሆንም ቡድኑ ያሳያቸውን ጥሩና ደካማ ጐኖች መመልከቱ ተገቢ ሆኖ ስላገኘነው እንደሚከተለው ዳሰነዋል፡፡

 

የብሔራዊ ቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ

አሠልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ እንዳለፉት ጨዋታዎች ሁሉ የ4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን (Formation) ይዘው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡ በዚህም ታሪክ ጌትነትን በግብ ጠባቂነት ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ስዩም ተስፋዬ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ አንተነህ ተስፋዬ እና ተካልኝ ደጀኔን በተከላካይነት እንዲሁም ራምኬል ሎክ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ሽመልስ በቀለን እና ኤፍሬም አሻሞን በአማካይ ቦታ ከነሱ ፊት ለፊትም ዳዊት ፈቃዱንና በረከት ይስሃቅን በአጥቂ ሥፍራ ተጠቅሟል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ በጉዳት ምክንያት ብሩክ ቃልቦሬ ተካልኝ ደጀኔን በመተካት ምንም እንኳን ተፈጥbዊ የግራ መስመር ተከላካይ ባይሆንም የቦታ ለውጥ ሳያደርግ በግራ ተከላካይነት ተቀይሮ ገብቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ አስቻለው በፊት አጥቂነት ይጫወት የነበረውን በረከት ይስሃቅን ቀይሮ የገባበት ሁኔታ ራምኬል ሎክን ወደፊት አጥቂነት ሲያመጣው አስቻለው የቀኝ መስመር የአማካይ ቦታን ሸፍኖ እንዲጫወት አድርጓል፡፡ የመጨረሻው ቅያሪ ወጣቱ ቢንያም በላይን በኤፍሬም አሻሞ ተክቷል፡፡ ይሄኛውን ቅያሬ እንደመጀመሪያው ሁሉ የተጫዋች እንጂ የቦታና የቅርጽ ለውጥ አላስከተለም፡፡ በአጠቃላይ በጨዋታው አብዛኛው ደቂቃዎች የጀመረበትን ቡድኑ የ4-4-2 አጨዋወት ተጠቅሟል፡፡

የመጀመሪያ አጋማሽ

ምናልባትም በአብዛኛው የጨዋታ ጊዜ የተጋጣሚው ቡድን ትክክለኛ ቅርጽ መዛባትን ስናስብ ጨዋታው ገና ከመጀመሩ የተቆጠረችውን ጐል ተፅዕኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ በአራቱ አማካዮችና በአራቱ ተከላካዮች መካከል የነበረው ክፍተት ስፋትን ተከትሎ ሽመልስ ሳይታሰብ ለዳዊት ያሻገረለትን ኳስ ዳዊት ፈቃዱ ከተጋጣሚው ኋላ ተነስቶ በመሮጥ ኳሷን ቀድሞ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ ከግቧም በኋላ የተጋጣሚው ቡድን ተጫዋቶች ያለመረጋጋት ችግር ታይቶባቸዋል፡፡ ይህም በጨዋታው ጅማሬ ላይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾቻችን የፈጠሩባቸው ጫና አላማ የሌላቸው ኳሶችን ከግባቸው ለማራቅ ብቻ በረጅሙ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ብሒራዊ ቡድን አብዛኛውን ደቂቃዎች ኳስንም በመያዝም ወደ ጐል በመቅረብም የተሻለ ነበር፡፡

የ4-4-2 አጨዋወት ከሚሰጠው ጥቅም አንዱ በሁለቱ የመስመር አማካዮች በሜዳው የጎን ሥፋት ወደ ጐን ጨዋታን በመለጠጥ የተጋጣሚን የመከላከል ቅርጽ ሰፊ ቦታ እንዲሸፍን በማስገደድ ክፍተት እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዋሊያዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ በግራ በኪል ያመዘነ ነበር፡፡ ይህም በኤፍሬም አሻሞ ኳስን እየገፉ በመሄድ እና ተጨዋቾችን የማለፍ ችሎታውን (Dribbling ability) በመጠቀም የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ በዚህ የኤፍሬም አጨዋወት ነፃ ሚና ከነበረው ሽመልስ በቀለና ከሁለቱ አጥቂዎች በጥቂቱ ወደ አማካዩ በመቅረብ ኳስን ለመቀበል ይሞክር ከነበረው አጥቂ በረከት ይስሃቅ ጋር አጫጭር ኳሶችን በፍጥነት ተቀባብሎ ወደ ተጋጣሚው ቡድን ሳጥን ውስጥ ለመግባት ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በተዛቡ የመጨረሻ ኳሶች እንዲሁም ባልተመጠነ የኳስ አገፋፍ (excessive dribbling) ምክንያት የግብ እድሎች ከመፈጠራቸው በፊት የሳኦቶሜ ተከላካዮች ያጨናግፏቸው ነበር፡፡ በሌላኛው መስመር በግራ በኩል ከነበረው እንቅስቃሴ በተቃራኒ ፈጣኑ ራምኬል ሎክ ኳስን በፍጥነት ይዞ በመግባትና ረዣዥም ኳሶችን ወደ ግብ በመላክ የተወሰኑ እድሎችን ለመፍጠር ሞክሯል፡፡

ከሁለቱ የመስመር አማካኞች ባለፈ ጋቶች ፓኖም እና በተለይም ሽመልስ በቀለ ባልተጠበቀ መልኩ ድንገተኛ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ አጥቂዎች ለማድረስ ሞክረዋል፡፡ ይህም ቡድኑ በአብዛኛው በአጫጭር ኳሶች ላይ የተመረኮዘ አጨዋወቱ በጣም ተገማች እንዳይሆን ረድቶታል፡፡ በጥቅሉ ቡድኑ በሦስቱም መንገዶች ተጋጣሚውን በማስጨነቅ ይፈጥራቸው የነበሩትን እድሎች ወደ ጐልነት መቀየር ተስኖታል፡፡

በዚሁ የመጀመሪያው አጋማሽ የሳኦቶሜ ብሔራዊ ቡድን አልፎ አልፎ በሁለቱ የግብ መስመሮች በተለይም በቀኝ መስመር በኩል ረዥም ኳሶችን ለመጣልና የግብ አጋጣሚን ለመፍጠር ከመሞከራቸው በቀር የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እጅጉን ደካማ ነበር፡፡ በተጨማሪም በዋልያዎቹ አማካዮች ላይ ጫና ያለመፍጠርና የኳስ መተላለፊያ ክፍተቶችን ለመዝጋትም ብዙም ጥረት አላደረጉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሽመልስ በቀለ ኳስን በነፃነት ማንሸራሸርን ክፍተቶችን እያየን የማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ነፃነት ሰጥቶታል፡፡

ሁለተኛ አጋማሽ

በሁለተኛውም አጋማሽ በድጋሚ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎቹ የተገኘችው የፍጹም ቅጣት ምት አጋጣሚ ጋቶች ፓኖም ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ ይህም የተጋጣሚው ቡድን አማራጭ እንዲጣና ከራሱ የግብ ክልል ወጥቶ ወደ ማጥቃቱ እንዲያተኩር አስገድደታል፡፡ ከጐሏ መቆጠር በኋላ በተለይም በመጀመሪዎቹ 25 ደቂቃዎች የሳኦቶሜ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለማጥቃት የተንቀሳቀሰበት ነበር፡፡ በዚህም ሳኦቶሜዎች እንደመጀመሪያው ግማሽ በመስመር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን መሀል ለመሀል ወደ ግብ በመጠጋትና ከርቀት አክርሮ በመምታት ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎች አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ የመከላከል ሽግግር (Defensive Transition) ላይ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን በመጠቀም በሁለቱም መስመሮች በተለይም በተደጋጋሚ በቀኝ መስመር በኩል ይዞ በመግባት እና ወደ መሃል በመጣል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በእነዚህ መንገዶች የፈጠሯቸው ጫናዎች የቆሙ ኳሶች እድልን አስገኝቶላቸው ነበር አልተጠቀሙባቸውም እንጂ፡፡

ይኸው የማጥቃት ሂደት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ሽመልስ በቀለን ወደ ጋቶች ፓኖም እንዲጠጋ እንዲሁም ኤፍሬም አሻሞን የቀኝ ማጥቃታቸውን ለመከላከል ወደ ብሩክ እንዲሳብ አድርጐታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የሳኦቶሜ ተከላካዮች የቡድኑን ማጥቃት በመከተል ወደ መሃል መስመር መቅረባቸው ከሽመልስና ከአስቻለው የሚነሱ ኳሶች ጥሩ የግብ አጋጣሚዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ኳሶች ወደ ጐልነት ለመቀየር ቢሳናቸውም የሳኦቶሜ አንደኛ የመሃል ተከላካይ ወደ መሃል መሳብ ለዳዊት የፈጠረለትን ክፍተት በዙሪያው አራት የተጋጣሚ ተጨዋቾችን ኳሱን በእግር ሥር በማቆየት ወደ ራሱ ከሳባቸው በኋላ አስቻለው ኳሱን ወደፊት ለቆለት ዳዊትም ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለራምኬ ሎክ ጐል ያበቃለት እድል ሰጥቶታል፡፡

 

ምስል 1፡ በ 74ኛ ደቂቃ 3ኛው ጎል የተፈጠረበት አጋጣሚ
ምስል 1፡ በ 74ኛ ደቂቃ 3ኛው ጎል የተፈጠረበት አጋጣሚ

ከዚህም በኋላ በተመሳሳይ ለሳኦቶሜ ተከላካዮች ወደ መሃል ሜዳው መቅረብና እንዲሁም ኳስን ለመቆጣጠል ሲሞክሩ በሚሰሩት ስህተት በተደጋጋሚ እድሎች ቢያገኙም ወደ ጐል መቀየር ግን አልተቻለም፡፡ በዚህ ሁለተኛ አጋማሽ የአማካኝ ሥፍራውን እንደ ኳሱ ፍሰት ቦታ እየቀያየረ ሲመራ ከነበረው ሽመልስ በቀለ በተጨማሪ የአስቻለውና በኤፍሬም ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ጥሩ የኳስ አገፋፍ ክህሎት ለተጨማሪ ጐሎች ምክንያት ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ በተጨዋቾቻችን የአጨራረስ ጥራት ችግር ምክንያት መክነዋል፡፡

በጨዋታው ላይ የነበሩ ደካማ ጎኖች እና የመፍትሄ ሐሳቦች

 

1. ግልፅ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን አለመጠቀም

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የአጨራረስ ችግር በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በዚህም ጨዋታ ላይ ይህ ችግር በተደጋጋሚ አጋጣሚዎች ተስተውሏል ፡፡ በጨዋተው እንቅስቃሴ ውስጥ የመከኑት ኳሶችን በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡

-የመጀመሪያው በቀላሉ ማስቆጠር ለሚችል ተጫዋች ኳስን ከመልቀቅ ይልቅ በችኩልነት ወደጎል መሞከር ነው (ምስል 2 እና ምስል 3) ፡፡

 

ምስል 2፡ 7ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ለበረከት ይስሀቅ እና ኤፍሬም አሻሞ የማቀበል አጋጣሚውን በቀጥታ ወደ ጎል በመሞከር ያመከነው ኳስ
ምስል 2፡ 7ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ለበረከት ይስሀቅ እና ኤፍሬም አሻሞ የማቀበል አጋጣሚውን በቀጥታ ወደ ጎል በመሞከር ያመከነው ኳስ

 


ምስል 3 ፡ 77ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ወደ ጎል በመሞከር ያመከናት ኳስ ከምትሞከር ይልቅ ለተመቻቸው ተጫዋች ቢያቀብለው በቀላሉ ግብ መሆን ይችል ነበር
ምስል 3 ፡ 77ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ወደ ጎል በመሞከር ያመከናት ኳስ

 

-ሁለተኛው ደግሞ ኳስን ለጎል ሙከራ ወይም አመቻችቶ ለማቀበል በትክክለኛው ቦታ እና ርቀት ላይ መሆኗን እርግጠኛ ባልሆኑበት አኳዃን ተቻኩሎ መሞከር ነው (ምስል 4 እና ምስል 5) ፡፡

 

ምስል 4 ፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ ወደ ጎል ለመምታትም ሆነ ወደ ግራ ለራምኬል ሎክ ለመስጠት የተመቸ ሁኔታ ላይ ከመሆኑ በፊት ወደ ግብ ሞክሮ ያመከናት ኳስ
ምስል 4 ፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ ወደ ጎል ለመምታትም ሆነ ወደ ግራ ለራምኬል ሎክ ለመስጠት የተመቸ ሁኔታ ላይ ከመሆኑ በፊት ወደ ግብ ሞክሮ ያመከናት ኳስ

 


image 5
ምስል 5፡ 83ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ግብ ጠባቂው ጋር ከመድረሱ በፊት ከፊቱ የነበረውን ሰፊ ክፍተት ኳሱን ለተሻለ የውሳኔ ቦታ ሳያመቻችበት በቀጥታ ሞክሮ ያመከነው የጎል አጋጣሚ

እነዚህ ችግሮች በተጨዋቾቻችን ልምድ እና የግል ክህሎት ላይ የተመረኮዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የተጠቀሱትን እክሎች ለማሻሻል ተጨዋቾቻችን ወደ መጨረሻው የማጥቃት ቀጠና በሚገቡበተ ጊዜ እና ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት በሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ራስን እና ኳስን በተገቢው መንገድ ተቆጣጥሮ አካባቢን በማስተዋል የተሻለ የማግባት እድል ላለው ተጨዋች መስጠት ወይም ትክክለኛውን የውሳኔ ሰዓት ጠብቆ ወደግብ የመሞከርን ክህሎት ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የሽግግር ችግሮች

ቡድኑ በሚያተጠቃበት ወቅት የተከላካይ መስመሩ በማጥቃት ላይ እየተሳተፉ ካሉ ተጠጨዋቾች ጋር ይፈጥረው የነበረው የሰፋ ርቀት በድንገት ኳስ ስትነጠቅ እና ወደ መከላከል ቅርጽ መመለስ በመያስፈልግበት ሰዐት ላይ ለ ተጋጣሚ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት መደራጃ የሚሆን ቦታ ይተው ነበር (ምስል 6) ፡፡

image 6
ምስል 6 ፡ 8ኛው ደቂቃ የኢትዮåያ ብሔራዊ ቡድን ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ላይ በተከላካዮች አና በአማካዮች መካከል የተወው ሠፊ ክፍተት ለመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ሲያጋልጠው

በተጨማሪም ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ወቅት ኳስን ወደተሻለ የማጥቃት ፍሰት ሊወስድ የሚችል ሰፊ ክፍተት እያለ የማጥቃት ጅማሬውን የተጋጣሚ ተጨዋቾች በብዛት ወዳሉበት እና በቀላሉ ማጨናገፍ ወደሚችሉበት አቅጣጫ መውሰድ ሽግግሮችን ከጅምራቸው እንዲበላሹ ሲያደርጋቸው ተስተውሏል (ምስል 7) ፡፡

image 7
ምስል 7፡ 27ኛው ደቂቃ የኢትዮåያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር በግራ በኩል ያለውን ክፍት ቦታ በመተው የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በብዛት በተገኙበት የቀኝ የሚዳ ክፍል በመጠቀም የጀመረው ያልተሣጋ የማጥቃት አጋጣሚ

የጨዋታ እንቅስቃሴ ወሳኝ አካል በሆኑት የሽግግር ጊዜዎች ላይ ተጫዋቾቻችን እንደየጨዋታ ክፍላቸው በአንድነት እና እንደየጨዋታ ቦታቸው በግል በተለይም ያለኳስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ሰፊ እይታን እና ትኩረትን እንዲያዳብሩ ማድረግ በጣሙን ወሳኝ ነው፡፡

 

ያጋሩ