” እግርኳስን አላቆምኩም የመጫወት አቅሙ አለኝ “
በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ያለፉት 20 ዓመታት ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ደጉ ደበበ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ብሔራዊ ቡድን ለ14 ዓመታት በመጫወት አይረሴ የሆኑ የስኬት ዓመታትን አሳልፏል። ባሳለፍነው ክረምት ግን ከፈረሰኞቹ ጋር መለያየቱን ክለቡ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ባበረከተው አስተዋፆኦ ልክ የክብር አሸኛኘት እንደሚደረግለት መግለፁም ይታወቃል።
ደጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከተለያየ በኋላ እግርኳስን ያቆማል ወይስ ወደ ሌላ ክለብ በማቅናት የእግርኳስ ዘመኑን ያሳልፋል የሚለው የብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰብ ጥያቄ ሆኗል። ደጉ የዘንድሮ ዓመት የሊጉ ውድድር ጅማሬ ላይ ቢገኝም እስካሁን በየትኛውም ክለብ እየተጫወተ አይገኝም። ይህን ተከትሎ ኳስ አቆመ ወይስ ምን አያቀደ ነው የሚገኘው የሚለውን ጥያቄ ሶከር ኢትዮጵያ ለደጉ አቅርባ በምላሹ በሰጠው አስተያየት በተጫዋችነት የመቀጠል ሀሳብ እንዳለው ተናግሯል። “በፍፁም እግርኳስን አላቆምኩም። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተለያየሁ እንጂ አሁንም የመጫወት ሙሉ አቅሙ አለኝ። ለተወሰኑ ጊዜያት ዕረፍት ለማድረግ በማሰብ ነው አንደኛው ዙር ላይ ያልተጫወትኩት። በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው በሁለተኛው ዙር ለአንዱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ እንደምጫወት ነው። ” ብሏል።
ደጉ የእግርኳስ ህይወቱ ጅማሮ በሆነው አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ የተሳካ ቆይታ ካደረገ በኋላ በ1996 ክረምት ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው። ከፈረሰኞቹ ጋር በቆየባቸው 14 ዓመታት ውስጥም 10 የፕሪምየር ሊግ (አምስቱ በአምበልነት)፣ 5 የአሸናፊዎች አሸናፊ እና 4 የኢትዮጵያ ዋንጫ በድምሩ 19 የዋንጫ ክብሮችን ሲያሳካ በግሉም ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊል ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን አግኝቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስም የቡድኑ አምበል ነበር።