በ2019 የቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጅቡቲ ቴሎኮምን በድምሩ 5-3 ማሸነፍ የቻለው ጅማ አባ ጅፋር የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት ከግብፁ አል አህሊ ጋር በሚጠብቀው የደርሶ መልስ ጨዋታ ነገ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ምሽት 02፡00 ላይ በአሌክሳንድሪያ ለሚደረገው ጨዋታም ተጫዋቾችን ጨምሮ 31 የልዑካን ቡድን አባላትን የያዘው የጅማ አባ ጅፋር ቡድን እኩለ ለሊት 06፡00 ላይ ወደ ካይሮ ለመብረር ዝግጅቱን አጠናቆ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ከሦስት ሠዓታት በረራ በኋላ ወደ ግብጿ መዲና ካይሮ ሲደርስ በመቀጠል በሚያደርገው ጉዞ ጠዋት 01፡00 ላይ አሌክሳንድሪያ እንደሚደርስ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኖቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊጉ ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ጨምሮ በቅድመ ማጣሪያውም ጭምር ምንም ሽንፈት አልገጠማቸውም። የነገ ተጋጣሚያቸው የግብፁ አል አህሊ ደግሞ በ2018ቱ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ከተሸነፈ በኋላ ከአረብ ሊግም የመሰናበት ዕጣ ቢገጥመውም በያዝነው የፈረንጆች ወር በአዲሱ አሰልጣኙ መሐመድ ዩሱፍ እየተመራ ያደረጋቸውን ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሲያሸንፍ አምስት ግብ አስቆጥሮ አንዴም መረቡን አላስደፈረም።
በአሌክሳንድሪያው ቦርግ አል አረበ ስታድየም የሚደረገውን ጨዋታ ቱኒዚያዊው ሳዶክ ሴልሚ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። እኚህ ዳኛ ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ጳጉሜ ወር ላይ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ያደረጉትን ጨዋታ የመሩ ናቸው። የሀገራቸው ዜጋ የሆኑት አይመን ኢስማኤል እና ሊቢያዊው አቲያ አምሳድ በረዳትነት የተመደቡት ዳኞች መሆናቸውም ታውቋል።