አቶ ኢሳይያስ ጅራ ስለ ሁለቱ ክልል ክለቦች ስምምነት…

ከአንድ ዓመት በላይ ለቆየ ጊዜ በትግራይ እና አማራ ክልል ክለቦች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ሲከናወኑ መቆየታቸው ይታወቃል። ትላንት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክለቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈው ስብሰባ የሁለቱ ክልል ክለቦች የእርስ በእርስ ጨዋታዎቻቸውን በየሜዳቸው ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተስፋ ፈንጥቋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት ከተረከቡ ጀምሮ ጉዳዩን መስመር ለማስያዝ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከክለቦቹ ስምምነት በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” በ2010 የሁለቱ ክልል ቡድኖች ጨዋታዎች በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከቡድኖቹ ጋር ተወያይቶ በገለልተኛ ሜዳ መጫወታቸው ትክክል ቢሆንም በ2011 ይህ እንዳይደገም ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ሒደት ውስጥም ከከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት እስከታችኛው ማኅበረሰብ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል። እኔ ፕሬዝዳንት ሆኜ ስመረጥም ሆነ ከዛም በፊት ሁሌም የምናገረው እና የነበረኝ አቋም ማንኛውም ቡድን ጨዋታውን በሜዳውና በደጋፊው ፊት ማድረግ አለበት የሚል ነበር። ይህን አቋም ሙሉ ለሙሉ የስራ አስፈፃሚው ተቀብሎት፤ ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ወደፊትም የሚደርግ ይሆናል።

” በሁለቱ ክልል ጨዋታዋች ያለመከናወናቸው መሰረታዊ ችግር የእግርኳስ ችግር አይደለም። ከጀርባ የነበረው ሌላ ጉዳይ ነው። ችግሩን ለመፍታት ብዙ ርቀት ተጉዘን ዛሬ ላይ ደስ በሚል መልክ የተጠናቀቀ ሲሆን የሁለቱም ክልል ቡድኖች አመራሮች በሜዳቸው መጫወት እንዳለባቸው በመግለፅ የፀጥታ እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን በሁለቱም ወገን ያሉ ቡድኖች አጥብቀው እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ተለያይተናል። ለሁላችንም እንዲህ ሰላማዊ እግርኳስ ሲኖር ነው በሰላም ለመምራት የምንችለው።

” በ2011 የሚደረገው ውድድር በሰላም እንዲጠናቀቅ የሁላችንም ፍላጎት መሆን አለበት። ሁሌም እግርኳሳችን እንዲያድግ የምንፈልግ ከሆነ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያስፈልገናል። ለዚህም ብሔራዊ ፌዴሬሽን በየአቅጣጫው ስራውን ጀምሯል። በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ የቡድኖች ደጋፊ ማኅበራትን ባለሙያ ልኮ ለማሰልጠን ፍቃደኛ ነው፤ ቡድኖቹ ዝግጁ የሚሆኑበትን ቀን አስቀድመው ቢያሳውቁን ፌዴሬሽኑ ባለሙያ በመላክ ስልጠናውን ያከናውናል። በቀጣይ የሁለቱም ክልል ክለቦች በተገኙበት ወይም በተናጠል መግለጫ በመስጠት እግር ኳሱን ሰላማዊ ማድረግ ያስፈልገናል። ሚዲያዎችም ገለልተኛ በመሆን እግርኳሳዊ አስተሳሰብን እና እግርኳስ የሚፈልገውን ነገር በማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠብቅባቸዋል። በስተመጨረሻ ይህ ሁሉ ልፋት እና ጥረት መሬት ወርዶ የታሰበለትን አላማ ሲያሳካ ማየት ነው የሁላችንም ፍላጎት ይህም እንዲሳካ ቡድኑቹ የወሰዱትን የቤት ስራ በአግባቡ መወጣት አለባቸው። እግር ኳስ የሰላም ተምሳሌት ነው የሚለውን በተግባር ማየት እንድንችል ፈጣሪ ይርዳን። “

ያጋሩ