የወልዋሎ እና ድሬዳዋ ጨዋታ በተያዘለት ቀን ይደረጋል

በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀ ግብር የወልዋሎ ዓ.ዩ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ቅዳሜ 9:00 ላይ ይደረጋል።

ነገ ከስድስተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ወልዋሎ መቐለ ላይ ድሬዳዋን እንዲያስተናግድ የወጣለትን መርሀ ግብር አስመለክቶ ከሦስት ቀን በፊት በደብዳቤ ያስገባው የጨዋታ ይራዘምልኝ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ጨዋታው ሊራዘም ይችላል ተብሎ ቢገመትም ክለቡ ከፌደሬሽኑ ጋር ከተነጋገረ በኋል ጨዋታው በተያዘለት ቀን እንዲደረግ ተወስኗል።
ባለፈው ሳምንት በብሔር ብሔረሰቦች በዓል ምክንያት ከመከላከያ ጋር ያደረገው ጨዋታ ወደ ሰኞ የተሸጋገረበት ወልዋሎ ለቅዳሜው ጨዋታ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ እንደሌው ገልጾ ነበር ጨዋታው እንዲራዘምለት የጠየቀው፡፡ ሆኖም ድሬዳዋ ቀድሞ ወደ መቐለ ከተማ በመግባቱ ቡድኑ ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረግ በማሰብ ጨዋታው በተያዘለት ቀን ቅዳሜ እንዲደረግ ሁለቱም አካላት ተስማምተዋል።

ወልዋሎ እና ድሬዳዋ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን አሸንፈው እንደመገናኘታቸው ብርቱ ፉክክር ይስተናገድበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ጨዋታ የነገው ብቸኛ የስድሰተኛ ሳምንት የሊጉ መርሀግብር ነው።

ያጋሩ