ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ነገ በብቸኝነት የሚደረገው የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ድሬዳዋ ከተማን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል። 

በትግራይ ስታድየም 09፡00 ላይ የሚደረገው የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በአምስተኛው ሳምንት ድል የቀናቸው ወልዋሎ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኛል። አምስት ግቦችን አስተናግደው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በመሸነፍ የጀመሩት ወልዋሎዎች በደቡብ ፖሊስ እና መከላከያ ላይ ያሳኳቸው የ1-0 ድሎች የውድድር ዓመታቸውን ጉዞ መጀመሪያ ያስተካከለው ይመስላል። በተመሳሳይ በአንደኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ተሸንፈው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከአርባ ሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ ባደረጉት የሊግ ጨዋታ ሳምንት ደደቢትን መርታት ችለዋል። በመሆኑም ከድል መልስ የሚገናኙት ሁለቱ ክለቦች በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ላይ መገኘታቸው ጨዋታውን ከጫና ነፃ ሆነው እንድያደርጉ እንደሚረዳቸው ይታመናል። 

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች አስራት መገርሳ ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው የሚደርስላቸው ሲሆን በመከላከያው ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ዋለልኝ ገብሬን ጨምሮ ሳምሶን ኃይለማርያም እና ዳንኤል አድሀኖም ግን አሁንም ቡድኑን እንደማያገለግሉ ታውቋል። በረከት ሳሙኤል ፣ አማረ በቀለ ፣ ምንተስኖት የግሌ ፣ ኃይሌ እሸቱ ፣ ሀብታሙ ወልዴ እና ዳኛቸው በቀለ ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ በመገኘታቸው ጨዋታው የሚያልፋቸው ይሆናል። 

በመከላከያው ጨዋታ ወደ ጥንቃቄ አድልተው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመጠበቅ የተጫወቱት ወልዋሎዎች ነገ በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ ግን እንደተለመደው ኳስን ከኋላ መስርተው መጫወትን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ይገመታል። የቡድኑ ማጥቃትም በአመዛኙ ወደ ኃላ እየተመለሰ ከአማካይ ክፍሉ ጋር የቅብብል መስመሮችን ሲፈጥር በሚታየው የመስመር አጥቂ ኤፍሬም አሻሞ በኩል የማድላት ዕድል ይኖረዋል። ይህ የሚሆን ከሆነ ከግብ ክልሉ እምብዛም ላይርቅ በሚችለው የድሬ የተከላካይ መስመር መሀከል ክፍተቶችን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ተጠባቂ ይሆናል። 

በድሬዳዋ በኩል ኢታሙና ኬይሙኒ እና ገናናው ረጋሳ ከቀጥተኛ ኳሶች የሚያገኟቸውን ዕድሎች ለመጠቀም ከወልዋሎ የመሀል ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ትኩረትን ይስባል። በተለይም የወልዋሎ የተከላካይ መስመር ከግብ ክልሉ ርቆ መጫወትን ምርጫው ካደረገ የኢታሙና ኬይሙኒ የመጨረሻ አጥቂነት ባህሪ ሊታይ የምችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ከዚህ ውጪ የብርቱካናማዎች የመስመር አማካዮች በተሻጋሪ ኳሶች ለሁለቱ አጥቂዎች የሚያደርሷቸው ኳሶች ተጨማሪ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች ግን ውዋነኛ ትኩረታቸው የወልዋሎ የግራ እና ቀኝ አጥቂዎችን መቆጣጠር ላይ መሆኑ የሚቀር አይመስልም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

– ወልዋሎ ሊጉን በተቀላቀለበት የ2010 የውድድር ዓመት የተደረጉት ሁለቱም የእርስ በእርስ ጨዋታዎች በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ፡፡

– በጨዋታዎቹ ደሬዳዋ ከተማዎች ያሸነፉት በተመሳሳይ 2-0 ውጤቶች በመሆኑ በድምሩ አራት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ወልዋሎዎች እስካሁን ግብ አልቀናቸውም፡፡

– ዓዲግራት ላይ የተደገው እና በዝናብ ምክንያት ተቋርጦ በቀጣዩ ቀን በቀጠለው የ30ኛ ሳምነት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን በሊጉ እንዲቆይ ያስቻለው ሲሆን ቡድኑ ከአንድ ዓመት ከሦስት ወራት በኋላ ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበውም ድል ነበር፡፡

ዳኛ

– በሁለተኛው ሳምንት ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡናን በመዳኘት አምስት የማስጠንቀቂያ ካርዶች የመዘዘው ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ ለመራት ተመድቧል። ተካልኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ስሑል ሽረ ጨዋታ ላይም አራተኛ ዳኛ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-3-3) 

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – አስራት መገርሳ – አፈወርቅ ኃይሉ

አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሀንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ሲላ አብዱላሂ – ራምኬል ሎክ

ኢታሙና ኬይሙኒ – ገናናው ረጋሳ