በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የግብፁ አል አህሊን የገጠሙ ጅማ አባጅፋር 2-0 ተሸንፏል።
ጅማ አባጅፋር ባለፈው ሳምንት በፕሪምየር ሊጉ ከስሑል ሽረ አቻ ከተለያየው ስብስቡ አክሊሉ ዋለልኝን በኄኖክ ገምቴሳ፣ ሲዲቤ ማማዱን በቢስማርክ አፒያ፣ ኤርሚያስ ኃይሉን በአስቻለው ግርማ ቀይረው ሲገቡ ባለሜዳው አል አህሊ ባለፈው ሳምንት ኤል ጋይሽን በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ለባዶ ካሸነፈው ስብስቡ አመዛኙን ተጠቅሟል።
ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ በሚያደርጓቸው መሃል ሜዳ ላይ በተገደቡ አጫጭር ቅብብሎች የጀመረው ጨዋታው ያለቀለት ግብ ሙከራ ያስተናገደው ገና በመጀመርያው ደቂቃ ላይ ነበር። አህመድ ሃሞውዲ ያሻማውን ማርዋን ሞህሰን በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት ሙከራ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ከመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በተለየ አጨዋወታቸው በተወሰነ መልኩ በመቀየር ወደሚታወቁበት ፈጣን የመስመር ማጥቃት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ያዞሩት አህሊዎች በሰባተኛው ደቂቃ መሪ የምታደርጋቸውን ጎል ማግኘት ችለዋል። በጨዋታው ለጅማ የግራ መስመር ፈተና ሆኖ ያመሸው የመስመር ተከላካዩ ካሪም ናድቬድ መቷት ብረቱን ለትማ የተመለሰችውን ኳስ ናስር መሃር ከጅማ ተከላካዮች መሃል ቀድሞ በመውጣት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረች ችሏል።
በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ከተጋጣምያቸው አንፃር የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ማሳካት የቻሉት ጅማዎች በመሃል ሜዳ የተሻለ የኳስ ፍሰት ቢያሳዩም ወደ ማጥቃት ወረዳ ለመግባት ሲቸገሩና በቁጥር ሲበለጡ ተስተውለዋል። መስዑድ መሃመድ መቶት ሸሪፍ ኢክረሚ በቀላሉ ካዳነው እና አስቻለው ግርማ መታት ወደ ላይ ከወጣችበት ሙከራ ውጭም ይህ ነው የሚባል ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ የሐምዲ እና የመስመር ተከላካዩ ናድቬድ ጥሩ መናበብን ተጠቅመው በርካታ የግብ እድሎች ፈጥረዋል። በተለይም ሐምዲ ከመስመር የተሻማችለት ኳስ በግምባሩ ገጭቶ አግዳሚው የመለሰበት፣ ከርቀት መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት እና ከሳጥን ውስጥ ከጥሩ አቋቋም ላይ ተገኝቶ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣባቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
በ38ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ሀሞውዲ ያሻገረውን ኳስ ለጅማ ተከላካዮች ጀርባውን ሰጥቶ የተቀበለው ማርዋን ሞሀሰን በመጀመርያ ንክኪ የተከላካዮችን ሚዛን በማሳት በጥሩ ሁኔታ ከዞረ በኋላ የመታው ኳስ በጅማ መረብ ላይ አርፋለች። ባለፈው ሳምንት ከኤል ጋይሽ ጋር በነበረው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሁለት ግቦች ያስቆጠረው ማርዋን ሞህሰን በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠርም ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያው ሁሉ የአል አህሊዎች የግብ ሙከራ የበላይነት የታየበት ሲሆን ቀያዮቹ በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አስቆጪ ሙከራዎችን አድርገዋል። ጅማዎች በአንጻሩ ከኳስ ቁጥጥር ያለፈ በጨዋታው ላይ ተፅእኖ ሊፈጥር የሚችል እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሐሚድ አሻምቷት ማርዋን ሞህሰን በግንባሩ ገጭቶ ባመከናት ወርቃማ እድል የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ከታዩ ሙከራዎች መካከል በ53ኛው እና 55ኛው ደቂቃዎች ከግራ መስመር አይመን አሽረፍ ያሻገራቸውና ማርዋን ሞሀሰን ከተመሳሳይ አቋቋም ሞክሮ የግቡ ብረት እና ዳንኤል አጄይ የመለሳቸው እድሎች የጅማ ጅፋርን እጅግ የወረደ የመከላከል አደረጃጀትን በጉልህ ያሳዩ ነበሩ። ተቀይረው የገቡት ሚዶ ጋብር እና ዋሊድ ሶሊማን ከግቡ ቅርብ ርቀት የማግባት አጋጣሚዎች አግኝተው በግቡ አግዳሚ እና በጅማ በኩል ጥሩ የተንቀሳቀሰው ዳንኤል አጄይ ግብ ከመሆን ያዳኑባቸው እድሎችም በዚህ አጋማሽ የሚጠቀሱ ነበሩ።
ጅማዎች በአንፃሩ በሁለተኛው አጋማሽ አስቻለው ግርማ ከርቀት ካደረገው ሙከራ ውጭ ለጎል የቀረበ ሙከራ ያላደረጉ ሲሆን አል አህሊዎች እንደወሰዱት ብልጫ እና እንደፈጠሩት የግብ እድል ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በአል አህሊ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጅማ አባ ጅፋርም የሁለት የጎል ልዩነቱን ቀልብሶ ወደ ምድብ ድልድል የመግባት ከባድ ፈተና በቀጣዩ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ይጠብቀዋል።