ግብጻዊው የሊቨርፑል አጥቂ መሐመድ ሳላህ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የቢቢሲ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
ሪከርድ የሆነ 650 ሺህ የቢቢሲ ተከታታዮች ድምፅ በሰጡበት በዚህ ሽልማት መሐመድ ሳላህ የናፖሊው ካሊዶ ኩሊባሊ፣ የቡድን አጋሩ ሳዲዮ ማኔ፣ የጁቬንቱሱ ሜሕዲ ቤናሺያ እና የአትሌቲኮ ማድሪዱ ቶማስ ፓርቴይን በመቅደም ነው አሸናፊ የሆነው።
ባለፈው የውድድር ዓመት ሮማን ለቆ ወደ ሊቨርፑል ካመራ በኋላ ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ሳላህ 44 ጎሎችን በቀዮቹ ማልያ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ሀገሩ ግብፅ ለ2018 የዓለም ዋንጫ እንድታልፍ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ሳላህ ከምርጫው በኋላ በሰጠው አስተያየት በድጋሚ ማሸነፍ አስደሳች ስሜት አለው። በቀጣዩ ዓመትም ማሸነፍ እፈልጋለው” ብሏል። ሊቨርፑል ዋንጫዎችን እንዲያሸንፍ መርዳትም የ2019 አላማው እንደሆነ ገልጿል።
መሐመድ አቦውታሪካ እና መሐመድ ባራካት በመቀጠል ምርጫውን በማሸነፍ ሶስተኛው ግብፃዊ መሆን የቻለው ሳላህ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በማሸነፍ ከአውስቲን ጄይ ጄይ ኦኮቻ ጋር ተስተካክሏል።