ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ከስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል በግዙፉ ባህር ዳር ስታድየም የሚደረገውን የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን ድል በማድረግ የፕሪምየር ሊግ ጉዟቸውን የጀመሩት ባህር ዳሮች ነገ ደግሞ ሌላኛውን የአዲስ አበባ ክለብ ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳቸው ያስተናግዳሉ። እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ያደረጉት ባህርዳሮች ከጊዮርጊሱ ድል በኋላ ከደቡቦቹ ሲዳማ እና ሀዋሳ ጋር ነጥብ መጋራት ችለዋል። ዘንድሮ ወደ ሊጉ ከመጡ ሌሎቹ ክለቦች በተሻለ ሁኔታም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሳምንት ወላይታ ድቻን ለማሸነፍ ከጫፍ ደርሰው በመጨረሻ በተቆጠረባቸው ግብ ነጥብ ለመጋራት የተገደዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከሊጉ መሪ ሀዋሳ ከተማ ጋር በነጥብ ዕኩል ሆነው መቀጠል ይችሉ የነበሩበትን ዕድል አምክነዋል። በመሆኑም እስካሁን ሽንፈት ያላገኛቸው ሁለቱ ክለቦች በሚገናኙበት ጨዋታ ባህር ዳር ሙሉ ነጥብ በማግኘት ከተጋጣሚው ጋር በነጥብ ለመስተካከል ቡና ደግሞ ሦስት ነጥብ ይዞ በመመለስ የሳምንቱን ውጤት ለማካካስ እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

የባህር ዳር ከተማ አማካይ መስመር ተጫዋቹ ዳግማዊ ሙሉጌታ አምና ቡድኑ በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደር በተጣለበት ቅጣት ምክንያት ነገም የማይሰለፍ ይሆናል። ባህር ዳር ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ቡድኑን በዋና አምበልነት ሲያገለግል የነበረው ነገር ግን በዘንድሮ የውድድር ዓመት በተጠባባቂ ወንበር ላይ እያሳለፈ የሚገኘው ደረጄ መንግስቱ ደግሞ በሃዘን ምክንያት ዕረፍት ተሰጥቶት ከጨዋታው ውጪ የሆነ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል። በሌላ በኩል ሣምንት ጉዳት ላይ ከነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች መካከል አህመድ ረሺድ እና ወንድይፍራው ጌታሁን ያገገሙ ሲሆን ግዙፉ አጥቂ ሱለይማን ሉኮዋ እና አስራት ቱንጆ ግን አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።

ከባህር ዳር አቀራረብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናም ከሜዳውም ውጪ በጣጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን የሚተገብር ከመሆኑ አንፃር ሲታይ የነገው ጨዋታ ፈጠን ያለ እና በሙከራዎች የታጀበ እንደሚሆን ይገመታል። ባህር ዳሮች ከኋላ ተመስረተው የሚመጡ ኳሶችን በዋነኝነት በዳንኤል ኃይሉ እና ኤልያስ አህመድ የአማካይ ክፍል ጥምረት ለሦስትዮሹ የፊት መስመር ጥምረታቸው ግብዓት የሚያደርጉ ይሆናል። ይህም ሁለቱ የማጥቃት አማካዮች ከዳንኤል ደምሴ እና አማኑኤል ዮሃንስ ጋር የሚገናኙባቸውን ቅፅበቶች እንድንጠብቅ ያደርገናል። ከዚህ በተጨማሪም በማጥቃት ላይ አብዝተው የሚሳተፉት የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮችም ከባህር ዳር የመስመር አጥቂዎች ከነ ግርማ ዲሳሳ ጋር ከባድ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜሱ ኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍሉን ሚዛን ለማግኘት ገና ይመስላል። ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው እና የቴክኒክ ብቃቱ ከፍ ያለው አልሀሰን ካሉሻ ከመጀመሪያ አሰላለፍ ሲወጣ መታየቱ በምን መልኩ ለቡድኑ ጉልበት ከሚሰጡት ከነዳንኤል ደምሴ ጋር ይጣመር የሚለውን ጥያቄ ወሳኝ አድርጎታል። በነገውም ጨዋታ ጋናዊው አማካይ በባህርዳር የአማካይ እና የተለላካይ መስመር መሀከል መንቀሳቀስ የሚችልበትን እና በተለይም ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር በቅብብል ሊገናኝ የሚችልበትን መንገድ ማግኘት ለቡናዎች የሚተው የቤት ስራ ነው። እነዚህን መስመሮች የመዝጋት እና የሚቋረጡ ኳሶችን ደግሞ ወደ ሁለቱ የማጥቃት አማካዮች ማድረስ ከባህርዳሩ የተከላካይ አማካይ ፍቅረሚካኤል አለሙ የሚጠበቅ ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ክለቦቹ በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ የሚገናኙበት የመጀመሪያው ጨዋታ ይሆናል።

– በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፍጻሜ ጥቅምት ወር ላይ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡

– ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች የአንድ ድል እና የሁለት አቻ ውጤቶችን ያሳካው ባህርዳር ከተማ ከአዲስ ግደይ የፍፁም ቅጣት ምት ውጪ በክፍት ጨዋታ እስካሁን ግብ አልተቆጠረበትም።

– ኢትዮጵያ ቡና እንደተጋጣሚው ሁሉ ሽንፈት ያልደረሰበት ሲሆን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ግብ አላስተናገደም ፤ ማስቆጠር ያልቻለው ደግሞ በአንዱ ጨዋታ ብቻ ነው።

ዳኛ

– እስካሁን ምንም ካርድ ካልተመዘዘባቸው ሦስት ጨዋታዎች መካከል በአራተኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ከአዳማ ከተማ ያደረጉትን ጨዋታ የዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ተስፋሁን ሸጋው – አሌክስ አሙዙ – ወንድሜነህ ደረጄ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ

ፍቃዱ ወርቁ – ጃኮ አራፋት –ግርማ ዲሳሳ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ቶማስ ስምረቱ – ተመስገን ካስትሮ – ተካልኝ ደጀኔ

ሳምሶን ጥላሁን – ዳንኤል ደምሴ – ካሉሻ አልሀሰን

አቡበከር ነስሩ – የኃላሸት ፍቃዱ – ሚኪያስ መኮንን