የስድስተኛው ሳምንት የሊጉ ብቸኛ መርሃ ግብር የነበረው የወልዋሎ እና ድሬዳዋ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
9:00 በጀመረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ከባለፈው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ዋለልኝ ገብሬን በአማኑኤል ጎበና ቀይረው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማዎችም በተመሳሳይ ደደቢትን ካሸነፈው ስብስባቸው ራምኬል ሎክን በወሰኑ ማዜ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በባለሜዳዎቹ ወልዋሎች ብልጫ የጀመረው ጨዋታው የጎል ሙከራ ያስተናገደው ገና እንደተጀመረ ነበር። በሙከራውም ኤፍሬም አሻሞ ከአፈወርቅ ኃይሉ የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ በግሩም ሁኔታ ሞክሮ ሳምሶን አሰፋ አድኖበታል። ብዙም ሳቢ ባልነበረው የመጀመርያ አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ወልዋሎች ከተጋጣምያቸው በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢያሳኩም ጠንካራውን የድሬዳዋ ከተማ መሀል ክፍል አልፈው ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም ሪችሞንድ አዶንጎ እና እንየው ካሳሁን በጥሩ ቅብብል ሄደው የድሬ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡት ወልዋሎዎች ከፈጥሯቸው ዕድሎች የተሻለ ሙከራ ነበር።
ቀሰ በቀስ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት ዕንግዶቹ ድሬዎችም በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከተጋጣያቸው በተሻለ ጠቅጠቅ ብለው ወደ ራሳቸው ሳጥን ተጠግተው በመከላከል በሁለቱ የመስመር ተጫዋቾቻቸው ለማጥቃት ሞክረዋል። በተለይም ከወሰኑ ማዜ በተሻለ የማጥቃት ነፃነት የነበረው በቀኝ መስመር የተሰለፈው ቆይቶም ከዋናው አጥቂው ጀርባ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሲላ አብዱላሂ ከሌሎች የቡድን አጋሮቹ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥሯል። ተጫዋቹ ከመስመር አክርሮ መቷት ኬታ አብዱልዓዚዝ ያዳናት ኳስ በድሬዎች በኩል ድንቅ ሙከራ ነበረች። ከዚህች ሙከራ ውጪም ዘነበ ከበደ እና ፍሬድ ሙሸንዲ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ።
እንደ መጀመርያው ሁሉ በተመሳሳይ ኤፍሬም አሻሞ ባደረገው ሙከራ የጀማረው ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን አምክነዋል።
በተለይም ሲላ አብዱላሂ ከጎሉ በቅርብ ርቀት ያገኛትን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ መትቶ ኬታ አብዱላዚዝ ያዳናት ድሬዎችን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ ዕድል ነበረች። ከዚህች ሙከራ ውጪም ፍሬድ ሙሸንዲ ከማዕዝን የተሻማችው ኳስ ከተጫዋቾች ጀርባ ብቻውን አግኝቶ ሞክሯት ግብ ጠባቂው ያዳናት አጋጣሚም ተጠቃሽ ናት።
ከዕረፍት መልስ ፕሪንስ ሰቨሪንሆን ቀይረው በማስገባት የተሻለ በመስመር ለማጥቃት ያሰቡት ወልዋሎዎች እምብዛም ቦታቸውን ለቀው የማይሄዱት የድሬ የመስመር ተከላካዮችን አልፈው ጫና ማሳደር ባይችሉም ለአጥቂው ኦዶንጎ በሚሻገሩ ኳሶች በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
በተለይም አዶንጎ ከአማኑኤል ጎበና የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ዞሮ መትቶ ሳምሶን በቀላሉ ያዳናት እና አማኑኤል ጎበና ከሳጥኑ በቅርበት ያገኛትን ኳስ አክርሮ መትቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰለት ኳስ ወልዋሎን የማታ ማታ ሦስት ነጥብ ለማስገኘት የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ወልዋሎዎች ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች በተጨማሪም አፈወርቅ ኃይሉ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እና ፕሪንስ ከርቀት አክርሮ ሳምሶን አሰፋ የመለሳት ሙከራ ይጠቀሳሉ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በጥብቅ እየተከላከሉ እና ሰዓት እያባከኑ የታዩት ድሬዎችም በመጨረሻው ደቂቃ አሸንፈው ለመውጣት ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው ምንያህል ይመር ያሻማው ኳስ ኢታሙና ኬይሙኒ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ቢገጭም ኬታ አብዱልዓዚብ በድንቅ ሁኔታ ወደ ውጪ አውጥቷታል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ያለግብ ተጠናቋል።
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ: LINK |