በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሽረ ላይ ስሑል ሽረ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 1-1 አጠናቀዋል። ስሑል ሽረ በሜዳው አሁንም ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
ከቀናት በፊት ሁለቱ ክለቦች በኢትዮጵያ ዋንጫ የተገናኙ ሲሆን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተዋል። ከረቡዕ ጨዋታም በርካታ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ገብተዋል። በሽረ በከል ሰዒድ ሁሴን፣ ደሳለኝ ደበሽ፣ መብራህቶም ፍሰሀ፣ ሙሉጌታ አንዶም፣ አሸናፊ ለማን በመተካት ኄኖክ ብርሀነ፣ ኄኖክ ካሳሁን፣ ንስሀ ታፈሰ፣ ዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ እና ልደቱ ለማ ሲገቡ በሲዳማ ቡናዎች በኩል ፍቅሩ ወዴሳ፣ ፀጋዬ ባልቻ፣ ሚካኤል ሀሲሳ፣ አበባየሁ ዮሀንስ፣ ጫላ ተሺታ፣ ተስፍ ኤልያስ፣ ሚሊዮን ሰለሞን እና ሰንደይ ሙቱኩን በማሳረፍ መሐመድ ናስር፣ ዳዊት ተፈራ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ዮናታን ፈስሀ፣ ፈቱዲን ጀማል እና አዲስ ግደይን በመጀመርያ አሰላለፍ አካተው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።
የስሑል ሽረ ቡድን አመራሮች ለእንግዳዎቹ ሲዳማዎች የሽረ ከተማ ምስል ያረፈበት ፎቶ በስጦታ በማበርከት የተጀመረው ጨዋታ ተደጋጋሚ አካላዊ ጉሽሚያ እና የዳኛ ፊሽካ የበዛበት ሲሆን ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ነበር የተጀመረው። በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ከግብ ክልል ቅርብ ርቀት ያገኙቱን የቅጣት ምት ፈቱዲን ጀማል በቀጥታ ቢመታም ግብ ጠባቂው ሰንደይ ሮቲሚ በጥሩ ብቃት ሊያድንበት ችሏል። ስሑል ሽረዎች ደግሞ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ልደቱ ለማ ከሚዲ ፎፋና የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካያቹ ሾልኮ በመውጣት ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መሣይ አያኖ በቀላሉ የተቆጣጠራት የመጀመርያ ሙከራ ነበረች። ከጉዳት ወደ ሜዳ የተመለሰው ንስሃ ታፈሰ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ የመታውና የግብ አግዳሚውን ጨርፎ የወጣው ኳስ የስሑል ሽረ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
ሲዳማዎች ከሽረ አንጻር በተጠና ሁኔታ ሲጫወቱ በ39ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ከወንድሜህ ዓይናለም የተሻማውን የማዕዘን ምት አዲስ ግደይ በግንባሩ ገጭቶ ሮቲሚ አድኖበታል። በ43ኛው ደቂቃ ላይ የስሑል ሽረ ግብ ጠባቂ ሰንደይ ሮቲሚ ቦታውን መልቀቁን ተከትሎ አዲስ ግደይ ያገኘውን ኳስ በግብ ጠባቂው አናት ላይ በማሳለፍ በግሩም አጨራስ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ የነበረው እንቅስቃሴ አሰልቺ ገፅታ የነበረው ነው። 57ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከመሐል መሬት ለመሬት የተላከለት ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ለመምታት ሲዘጋጅ የስሑል ሽረ ግብ ጠባቂ ሰንደይ ሮቲሚ ቦታውን ለቆ በመውጣት ሊያድንበት ቻለ እንጂ የሲዳማን የግብ መጠን ሊያሳድግ የሚችልበት አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። በመጠኑም ቢሆን የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ ብርቱ ትግል ያደረጉት የስሑል ሽረ ተጫዋቾች በ67ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። ልደቱ ለማ ከኄኖክ ብርሃኑ የተሻገረለትን ረጅም ኳስ ወደ መሬት በማውረድ በቀጥታ ወደ መትቶ ከመረብ አሳርፎታል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ከባድ የሚባሉ አጨዋወቶች ሲስተዋሉ ጨዋታው ወደ መጠናቀቁ አካባቢ በሲዳማ ቡና በኩል ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፀጋዬ ባልቻ ከአዲስ ግደይ የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ሰንዴይ ሮቲሚ እንደምንም በግቡ አናት ያወጣት ኳስ ለሲዳማ አስቆጪ ነበረች። ጨዋታውም በዚህ መልኩ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በስታዲየሙ የተገኙ ደጋፊዎች በእለቱ ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቃገኘው ውሳኔዎች ላይ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞችም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።