የአስልጠኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 ደቡብ ፖሊስ

ወላይታ ድቻ ሶዶ ላይ ደቡብ ፖሊስን አስተናግዶ 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የሁለቱ ከለቦች አሰልጣኞች አሰነያየታቸውን ሰጥተዋል። 
” አሁንም ማስተካከል የሚገቡን ነገሮች አሉ” ዘነበ ፍስሃ

ስለ ጨዋታው እና ስለድላቸው

“ጨዋታው ደርቢ እንደመሆኑ መጠን ከባድ እንደሚሆን ገምቼ ነበር። ሲጀመር አከባቢ 15 እና 20 ደቂቃ ጥሩ አልነበርንም። በኋላ ላይ ነው ወደ እንቅስቃሴው የገባነው። ጨዋታው እንደሚከብደን ስላወቅን ተጠንቅቀን ነበር የገባነው። ስለዚህ ባገኘነው ውጤት በጣም ደስቸኛ ነኝ። አሁንም ማስተካከል ያለብን ነገሮች አሉን፤ ቡድኔ እንደምፈልገው እስካሁን አልመጣልኝም። ይሄ ድል ለቀጣይ ጨዋታችን የሞራል ስንቅ ነው የሚሆነን።”

የግብ እድል ስላለመፍጠራቸውና ስለ ተጋጣሚያቸው

“የግብ እድል የመፍጠር ችግር አለብን። በቅንጅት የሚመጣ ነገር ስለሆነ ልምምድ ላይ እየሰራን ነው ። ጨዋታ ላይ ባይመጣልንም ደጋግመን እንሞክረዋለን። ተጋጣሚያችን ደቡብ ፖሊስ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። ሰዎች ቡድኑ ነጥብ ስለጣለ ቀላል ግምት ሰጥተውት ነበር። ሜዳ ላይ የታየው ግን እጅግ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው።”

ተከታታይ የሜዳ ድል እና የተሰላፊዎች መለዋወጥ 

“በሜዳችን ላይ ሁለት ጨዋታዎች ድል አድርገናል የ። ይህንን ማድረግ ከቻልን ደሞ ከሜዳችን ውጪም ማሸነፍ የማንችለበት ምንም ምክንያት የለም። ሰለዚህ ከሜዳ ውጪ ለማሸነፍ እንጥራለን። (ሰለ ቋሚ አሰላለፍ) በዕለቱ የምመርጣቸወ ተጫዋቾቼ ለኔ ቋሚ ናቸው። ፤ በኔ ቡድን ውስጥ ሁሉም ተጫዋቾች ቋሚ ናቸው። እንደየጨዋታው በምፈልገው መንገድ እያቀያየርኩኝ ነው የምጠቀማቸው።”


” አቻ ለጨዋታው ተገቢ ውጤት ነበር ” ዘላለም ሽፈራው – ደቡብ ፖሊስ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር። በሁለታችንም በኩል ብልጭ ድርግም የሚል እንቀስቃሴዎች ነበሩ፤ ወደ ጎል ከመድረስ አንፃር ምናልባት ማጋነን ባይሆንም እኛ ከነሱ የተሻልን ነበርን። በ90 ደቂቃ ውስጥ አንድም ሙከራ አላደረጉም፤ ግብ የተቆጠረችብንም በራሳችን ስህተት ነው። በጨዋታው ግብ ለማግኘት ጫና ለመፍጠር ሞክረናል። ጎል ከገባብንም በኋላ ጫና ፈጥረናል። ለኛ ሽንፈቱ አይገባንም፤ አቻ አስታራቂ ውጤት ነበር በእኔ እይታ

የዛሬው ተጋጣሚያችን ለኛ አስቸጋሪ አልነበረም። ምክንያቱም አስቸጋሪ ተጋጣሚ ማለት ተደጋጋሚ ግብ መሞከር ሲችል እና እንዳታስቆጥር ሲያግድህ ነው። ለኛ በዛሬው ጨዋታ ወላይታ ድቻ ጥሩ አይደለም፤ አልከበደንም። የኛ ችግር ነው በአጠቃላይ። ይህ ማለት ግን ሽንፈቱን ላለመቀበል አይደለም።”

ጎል የማስቆጠር ችግር

“እውነት ነው ጎል የማስቆጠር ችግር አለብን። እዚህኛው ጨዋታ ላይ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ በፊትም በነበሩን ጨዋታዎች በርካታ እድሎች አግኝተን ማስቆጠር አልቻልንም። ይሄ ችግራችንን ለመቅረፍ እንሰራለን። ”

ከውጤት ማጣት ስለመውጣት

” በርግጥ 5 ጨዋታዎች 3 ነጥብ መያዝ በአንፃራዊነት ጥሩ የሚባል አይደለም። ቡድኑ ዘንድሮ ነው የመጣው እና ዋንጫ ለማንሳት አይደለም የሚጫወተው፤ በሊጉ ለመሰንበት ነው እቅዳችን። ችግራችን ሜዳችንም ላይ ከሜዳችንም ውጪ ነጥብ መያዝ አልቻልንም። ይህንን ደሞ ጠንክረን በመስራት ነው የምንቀይረው። በርግጠኝነት ይሄንን ሰርተን እንቀለብሳለን።”