ከፍተኛ ሊግ | የሦስተኛ ሳምንት ምድብ ሀ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ተከናውነው ወልዲያ ከሁለት ተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ ሲጥል ኤሌክትሪክ እና ለገጣፎ አሸንፈው ነጥባቸውን ከወልዲያ ጋር አስተካክለዋል። 

ጎፋ አካባቢ በሚገኘው የልምምድ ሜዳው አማራ ውሀ ስራ (አውስኮድ)ን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸንፏል። የኤሌክትሪክን ብቸኛ የድል ጎል ያስቆጠረው ከሳምንታት በፊት ቡድኑን በውሰት የተቀላቀለው ተከላካዩ ዮሀንስ ዘገየ በ7ኛው ደቂቃ ነው። ድሉ ኤሌክትሪክን ከሶስት ጨዋታ 7 ነጥቦች እንዲሰበስብ አድርጎታል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ወደ ደሴ አምርቶ ደሴ ከተማን 1-0 በማሸነፍ እንደ ወልዲያ እና ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ ላይ ደርሷል። የለገጣፎን ብቸኛ የድል ጎል በ32ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ሐብታሙ ፍቃዱ ነው።

ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ ከወልዲያ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የውድድር ዓመቱን በሁለት ተከታታይ ድል የጀመረው ወልዲያ ነጥብ ቢጥልም የምድብ ሀን አሁንም በግብ ልዩነት እየመራ ይገኛል።

ኒያላ ሜዳ ላይ ላይ አቃቂ ቃሊቲ አክሱምን ገጥሞ በሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ገሎች 2-1 አሸንፏል። በ56ኛው ደቂቃ ሳምሶን ተሾመ፤ በ85ኛው ደቂቃ አብድልሀሚድ ሰዒድ የአቃቂ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ዓመቱን በሽንፈት የጀመረው አቃቂ ቃሊቲ ሁለት ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ ችሏል።

ዱከም ላይ ገላን ከተማ ከወሎ ኮምቦልቻ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ሁለቱም ቡድኖች እስካሁን ድል ማስመዝገብ ካልቻሉ ቡድኖች መካከል ናቸው።

ሰበታ ላይ በሰበታ ከተማ እና ፌዴራል ፖሊስ መካከል የተደረገው ጨዋታ በውዝግቦች ታጅቦ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው መሐል ከ30 ደቂቃዎች በላይ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ስለ ጉዳዩ ከተለያዩ አካላት ለማጣራት ሙከራ አድርጋለች።
ከስፍራው ከነበረ ምንጫችን የሚከተለውን መረጃ ነግሮናል። ” ጨዋታው ላይ ኳስ በፌዴራል ፖሊስ የግብ ክልል ውስጥ በእጅ ተነክቶ የፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጥ ቀርቷል። በእጅ ቢነካም ውሳኔው ግን የዳኛው ነው። የሰበታው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ስሜታዊ ነበር። ውስን ደጋፊዎች ወደሜዳ ቢገቡም ወዲያው ነው የወጡት። የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኃላፊነቱን እንወስዳለን ቢልም የእንግዳው ቡድን አሰልጣኝ ልዩ ኃይል ሳይመጣ አንጫወትም በማለቱ ጨዋታው ተቆርጦ ነበር። የፌዴራል ፖሊስ ተጫዋቾችም ብዙ ጊዜ ሜዳ ላይ ሲወድቁ ነበር።” ብሎናል።

የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በበኩላቸው ተከታዩን አስተያየት ሰጥተውናል። ” በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ዓመት ቆይቻለው፤ ኳሳችን እንዲያድግም እፈልጋለሁ። ለእሱም ጠንክሬ እየሰራው ነው። በዛሬ ጨዋታ በተጫዋቾቼ ጥረት ኮርቻለሁ፤ የተቻላቸውን አድርገዋል። ተከሰተ የተባለሁ ነገር አቤል አክርሮ የመታው ኳስ በእጅ ቢነካም ፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጥ ቀርቷል። ከዚያም በተጨማሪ ኢብራሂም ከድር ፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ ተጠልፎ ምንም አይነት ነገር አላየንም። በዚህም ምክንያት ደጋፊው ትንሽ ቆጣ ያለ ይመስለኛል። እረፍት ሰዓት ላይ የተወሰኑ 3 ወይም 4 ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ነበር። ነገር ግን በነበረው የፀጥታ ኃይል እና በእኛ አስተባባሪነት ደጋፊው ተረጋግቶ ጨዋታው እንዲቀጥል ቢባልም ከተጋጣሚያችን ልዩ ኃይል ይምጣ በሚል ጥያቄ ከ30 ደቂቃ በላይ ቆመናል። ይህ ደሞ በእንቅስቃሴ ላይ የነበረ ሰውነት ትንሽ ይጎዳል።

” እግር ኳስ ስሜታዊ ያደርጋል። እንደተባለው በጣም ስሜታዊ ሆኜም አልነበረም፤ በእርግጥ ትንሽ የሆነ ብስጭት ቢታይብኝ እግርኳስ የሚፈጥረው ነው።” ብለዋል።