የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ሲከናወኑ በምድብ ሐ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ሀዲያ ሆሳዕና፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሺንሺቾ ድል አስመዝግበዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና በሜዳው ቡታጅራ ከተማን አስተናግዶ 3-0 በማሸነፍ ነጥቡን ስድስት አድርሷል። ኬንያዊው አንጋፋ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ በሆሳዕና ማልያ የመጀመርያ ጎሉን ሲያስቆጥር የቀድሞ የወላይታ ድቻ ተጫዋች ዳግም በቀለ እንዲሁም ከሀላባ ዙንድሮ በለድኑን የተቀላቀለው ስንታየሁ አሸብር ሌሎቹን ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
የመጀመሪያውን ጨዋታ በሜዳው ያደረገው አዲስ አዳጊው ከምባታ ሺንሺቾ ስልጤ ወራቤን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። የሺንሺቾን ቦቸኛ የድል በ85ኛው ደቂቃ ማስቆጠር የቻለው ብርሃኑ ነው።
የቀድሞ የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን አርባምንጭ ላይ ያገናኘው የአርባምንጭ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታ በባለሜዳው 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አለለኝ አዘነ የሁለቱ ግቦች ባለቤት ነው።
በሌሎች ጨዋታዎች ነጌሌ ቦረና ከ ከፋቡና ባደረጉት ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ ነቀምት ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተለያይተዋል። ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከ ቤንች ማጂ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ደግሞ ቢሾፍቱ መሳተፍ አለመሳተፉ ገና ባለመረጋገጡ ሳይደረግ ቀርቷል።