ትላንት በተፈጠረ የደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ጨዋታው ከመከናወኑ በፊት የተቋረጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ዛሬ እንዲደረግ የሊግ ኮሚቴው ውሳኔውን አሳለፈ፡፡
በስድስተኛ ሳምንት ትላንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊደረግ መርሀ ግብር ወጥቶለት የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ጨወታ ከጨዋታው አስቀድሞ በተፈጠሩ የደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ያልተገቡ ትዕይንቶችን ካሳየን በኋላ ጨዋታው ሳይደረግ ማደሩ ይታወሳል። ትላንት ይህ ጨዋታ ለዛሬ 9 ሰዓት በዝግ ስታዲየም እንዲደረግ የዕለቱ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች መወሰናቸው የሚታወስ ቢሆንም የሀዋሳ ከተማ ክለብ “ተጫዋቾቼ ተጎድተውብኛል፤ ደጋፊዎቻችንም ጉዳት ገጥሟቸዋል፤ አንጫወትም” በማለት ዛሬ ማለዳ ወደ ሀዋሳ ጉዞ በመጀመራቸው ጨዋታው የመደረጉ ነገር አጠራጥሮ ነበር።
አሁን ደግሞ አይደረግም ሲባል የነበረው ጨዋታ እንደሚደረግ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል። ዛሬ 4 ሰዐት ላይ በተደረገ የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይ በተያዘለት ሰዓት እንዲደረግ የተወሰነ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በቦታው ሲገኙ በጉዞ ላይ የነበሩት የሀዋሳ ከተማ ተወካዮች አልተገኙበትም። ይሁንና ባቱ ከተማ (ዝዋይ) ደርሰው የነበሩት ሀዋሳዎች ፌድሬሽኑ አስቸኳይ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያን ለክለቡ በመላኩ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ ሲገኙ በአሁኑ ሰዓት ዐለም ጤናን እያለፉ መሆኑ ታውቋል። በዚህም ጨዋታው ምናልባትም ሀዋሳ በጉዞ ላይ ከመሆኑ አንጻር በአንድ ሰዓት ተግፍቶ 10 ሰዓት ላይ በዝግ ስታዲየም እንደሚከናወን ይጠበቃል ።
-በጉዳዩ ዙርያ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተልን እናቀርባለን