ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ዙር አለፈ

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ፓፓዋ ኒው ጊኒ ለምታዘጋጀው የአለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታውን ከቡርኪና ፋሶ አቻው ጋር አድርጎ 0-0 የተለያየ ሲሆን በድምር ውጤት 2-0 በማሸነፍ ወደ መጨረሻው ማጣሪያ አልፏል፡፡
በመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር የተበለጠው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኳሶችን ወደ ጎል የመሞከር እንዲሁም የተገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት የመቀየር ችግር ታይቶበታል፡፡ ኳሶችን አደራጅቶ የቡርኮና ፋሶን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት የተቸገረው የአሰልጣኝ አስራት አባተ ቡድን በ33 እና 34ኛው ደቂቃ በሎዛ አበራ አማካኝነት ሁለት ያለቀላቸውን የግብ ዕድሎች አምክኖል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ዋጋዱጎ ላይ ለቡርኪና ፋሶ ያልተሰለፈችው ሳኑጎ ማዉሎታ በኩርኪና ፋሶ በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችላለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሸሎ በታየበት የሁተኛው አጋማሽ ጨዋታ 4 ያክል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርጓል (49ኛው አዲስ ንጉሴ፣ 61ኛው፣ 62ኛው፣ 76ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ)፡፡ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የቡርኪና ፋሶን ተከላካይ መስመርን ለመስበር ያልተሳካ ሙከራ አድርጓል፡፡ በጨዋታው ላይ የቡርኪና ፋሶ ተጫዋቾችን በአካል ብቃት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሸሎ ተገኝቷል፡፡
ከጨዋታው በኃላ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ አስራት አባተ ያገኟቻን ዕድሎች አለመጠቀማቸውን ገልፀዋል፡፡
“የዛሬው ጨዋታ እንደጠበቅነው ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቀናል ብለን እንደገመትነው በጨዋታው ላይም ከፍተኛ ፉክክር ገጥሞናል፡፡ ጨዋታው ከብዶናል ማለት አይቻልም፡፡ በባለፈው ጨዋታ ላይ ያልነበሩ ሁለት ተጫዋቾችን ቡርኪናዎች ተጠቅመዋል (ሳኑጎ ማዉሎታ እና ትራኦሬ ኮሮቱማ)፡፡ እግርኳስ እሰከሆነ ድረስ ያሉብንን ችግሮች ለመቅረፍ ተግተን እንሰራለን፡፡” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ ኢኳቶሪያል ጊኒን ያሸነፈችውን ጋናን አዲስ አበባ ላይ በመጨረሻው ማጣሪያ ይገጥማል፡፡

ያጋሩ