የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ሀዋሳ ከተማ 

ትላንት እንዲካሄድ መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረውና ከበርካታ ንትርኮች በኋላ ዛሬ በ9 ሰዓት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በዝግ በተከናወነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

” ጨዋታው መዘዋወሩ ከእኛ በተሻለ ለእነሱ ተመችቷቸዋል” ስቴዋርት ሃል – ቅዱስ ጊዮርጊስ 

ስለጨዋታው

“በእርግጥ ጨዋታውን ተቆጣጥረን መጫወት ችለናል። በጨዋታው አስቆጥረናት በተሻረችብን ግብ እጅጉን አዝነናል፡፡ ከተጫዋቾቼ ከዚህ በላይ ጥረትና ስራ መጠየቅ አልችልም፤ የቻሉትን በሙሉ ሰጥተው ተጫውተዋል፡፡ ሙሉ 90 ደቂቃ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥረት አድርገናል። በአንጻሩ እነሱ ለማሸነፍ አልመጠጡም፤ አቻን ፈልገው ነበር የመጡት። በጨዋታው እኛ ብቻ ነበርን ለማሸነፍ ስንጫወት የነበርነው። ቅያሪዎቻችን በሙሉ ጨዋታውን ለማሸነፍ የተደረጉ ነበሩ፡፡ የሚረብሹ ሁለት ቀናትን ነበር ያሳለፍነው ፤ ደጋፊዎቻችን ሳንይዝ መጫወታችን ትልቅ ጥቅም አሳጥቶናል፡፡ሶስት አጥቂዎቻችን ጉዳት ላይ መሆናቸው ግብ ማስቆጠሩ ላይ ችግር ፈጥሮብናል፡፡”

ስለ ጨዋታው ወደ ዛሬ መዞር 

“ጨዋታው መዘዋወሩ ከእኛ በተሻለ ለእነሱ ተመችቷቸዋል ፤ እኛ በትልቁ ደጋፊዎቻችንን አጥተናቸዋል። በተጨማሪም እኛ ለትላንቱ ጨዋታ በደንብ ተዘጋጅተን ነበር። ይህ አፍሪካ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ በ4 የተለያዩ አህጉራት ሰርቻለሁ፤ ከሁሉም ግን ፈታኙ አፍሪካ ነው። አፍሪካ ለጀግኖች እንጂ ለደካሞች ቦታ የላትም፡፡ የተፈጠረውን ችግር ለራሳቸው ጥቅም በሚመች መልኩ ተጠቅመውበታል፤ ይህንን እንደሚሆን ገምተን ነበር፡፡”

“የተጫወትንበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነበር” አዲሴ ከሳ- ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“ውጤቱ ለእኛ ጥሩ ነው፤ የተጫወትንበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነበር። ጨዋታውን ትተን ወደ ሀዋሳ እየተጎዝን ከዝዋይ ተመልሰን እንደመጣን ነበር ወደ ጨዋታው የገባነው፡፡”

ጨዋታው ዛሬ መደረጉ እየታወቀ ስለመሄዳቸው

“እኛ እየጠበቅን የነበረው እንደዚህ አይነት ጨዋታ ሲቋረጥ በዝግ ስታዲየም ብቻ መደረጉን አልነበረም ፤ ከ150 ኬሎ ሜትር ባላነሰ በገለልተኛ ሜዳ ይደረጋል ብለን ነበር ስናስብ የነበረው፡፡ በተጨማሪም የጨዋታው ውሳኔ በዚህ መልኩ ይፈጥናል ብለን አላሰብንም። ይባስ ብሎ የተነገረን በቃል ነበር፤ ይህም በደብዳቤ እስካልተገለጸልን ድረስ አግባብ ስላልነበር ከዚህ የተነሳ ሄደናል፡፡”

ጉዳት ስለደረሰባቸው ተጫዋቾች 

“በትክክል ጉዳት ነበር፤ የተጎዱት ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በሚገቡበት ወቅት ተከትለዋቸው የመጡት ደጋፊዎች ሽሽት የኛ ተጫዋቾች መሀል ገብተው ነበርና ያንን ለማረጋጋት ጥረት ያደረጉ ተጫዋቾች ተጎድተውብናል። ከነዚህም መካከል መሣይ ጳውሎስ እና ግብ ጠባቂያችን ሜንሳህ ይገኝበታል፡፡”