ቻን 2016 ፡ ለመልሱ ወሳኝ ፍልሚያ ተጨማሪ ተጫዋቾች ተጠርተዋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን 2016 ለማለፍ ከባድ ፈተና ከፊቱ ተጋርጧል፡፡ ከቡጁምቡራ 2-0 ተሸንፎ የተመለሰው ብሄራዊ ቡድናችን እሁድ ምሽት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን እረፍት አድርገው ዛሬ ረፋድ ላይ ልምምድ አድርገዋል፡፡ በመጪው እሁድም የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

በዛሬው ልምምድ ላይ 16 ተጫዋቾች ሲገኙ በቡሩንዲው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው ኤፍሬም አሻሞ ፣ ጉዳት ላይ የሚገኙት ዘካርያስ ቱጂ እና ተካልኝ ደጀኔ ፣ የእጅ ጉዳት ያጋጠመው ዳዊት ፍቃዱ ልምምድ አልሰሩም፡፡

በረፋዱ ልምምድ ላይ ጠንካራ የአካል ብቃት ስራዎችን ያሰሩት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በጉዳት እና ቅጣት እንዲሁም በተገቢነት ጉዳይ (ሽመልስ በቀለ በቻን መሰለፍ አይችልም) ያጧቸውን ተጫዋቾች ለመተካት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል፡፡

ዘካርያስ እና ተካልኝ በመጎዳታቸው በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ የተጫዋች እጥረት የገጠማቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለመከላከያው ነጂብ ሳኒ ጥሪ አድርገውለታል፡፡ ነጂብ 2008 ከገባ ጀምሮ ለመከላከያ በኢትዮጵያ ዋንጫ እና አምበር ዋንጫ ላይ ጥሩ እንቅስቀሴ ሲያደርግ የነበረ የግራ መስር ተከላካይ ነው፡፡

በፊት መስመር ላይ ዳዊት ፍቃዱ በመጎዳቱ በድንቅ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው መሃመድ ናስር ጥሪ ተደርጎለታል፡፡ መሃመድ ከጉዳት መልስ ለመከላከያ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡

አሁን ባለው ስብስብ የሽመልስ በቀለ ቀጥተኛ የቦታው ተተኪ ያልያዙት ዮሃንስ ሳህሌ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ቡናው ኤልያስ ማሞ እና የመከላከያው ፍሬው ሰለሞን አዙረዋል፡፡ የአጥቂ አማማካዩ ኤልያስ በአሰልጣኝ ፖፓዲች ስር በግራ መስመር አማካይነት እየተጫወተ ሲሆን ከ2013 የሴካፋ ውድድር በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ተመርጧል፡፡ የውድድር ዘመኑን በድንቅ አቋም የጀመረው ፍሬው ሰለሞን ደግሞ የሽመልስን ቦታ ይዞ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዳዲስ የተመረጡት ተጫዋቾች ዛሬ ከሰአት ቡድኑ በሚያደርገው የቀኑ ሁለተኛ ልምምድ ላይ ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምድ ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ከዛሬ ረፋድ ልምምድ የተወሰደ
ከዛሬ ረፋድ ልምምድ የተወሰደ

 

ያጋሩ