በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን አራተኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ንፋስ ስልክ እና መቐለ ድል ሲቀናቸው ልደታ እና ፋሲል እንዲሁም ሻሸመኔ እና አቃቂ ነጥብ ተጋርተዋል።
የአአ ስታድየም ውሎ
በዳዊት ፀሐዬ
በአዲስ አበባ ስታድየም በቅድሚያ 9፡00 ላይ ልደታ ክፍለ ከተማን ከፋሲል ከነማ ባገናኘው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ሳይሸናነፉ 0-0 ተለያይተዋል። ባለሜዳዎቹ ልደታ ክፍለ ከተማዎች የተሻሉ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ምንም እንኳን ግብ ማስቆጠር ባይችሉም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ጎል መድረስ ችለዋል ፤ በተለይም 10 ቁጥር ለባሿ ዕድላዊት ለማ ከመስመር እየተነሳች በተደጋጋሚ አደገኛ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችላለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተመሳሳይ መልኩ እምብዛም ማራኪ ያልነበረ እንቅስቃሴ አሳይተዋል ፤ በዚህም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስመለክተን ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው ጨዋታ የተገናኙት ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ቦሌ ክፍለ ከተማ ነበሩ ፤ በጨዋታው ንፋስ ስልኮች 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ከዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ በተሻለ ጠንካራ ፉክክር ታይቶበታል። በዚህም በ17ኛው ደቂቃ ማርታ አያኖ ንፋስ ስልክን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችላለች። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ደግሞ ንፋስ ስልኮች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት እየሩሳሌም ወንድሙ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች።
59ኛው ደቂቃ ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማዎች ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ትዕግስት ኃይሌ አስቆጥራ ቡድኗን ወደ ጨዋታው ልትመልስ የምትችልትን ዕድል ፈጥራ ነበር ፤ በዚህ ግብ የተነቀቃቁ የሚመስሉት ቦሌዎች በተደጋጋሚ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ ነገር ግን ንፋስ ስልኮች በ82ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ካገኙትን ኳስ እየሩሳሌም ወንድሙ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ደግሞ ሦስተኛዋ እና የማሳረጊያዋን ግብ አስቆጥራ የቡድኗን የበላይነት አስጠብቃ ጨዋታው ተጠናቋል።
መቐለ 2-1 ቂርቆስ
በማቲያስ ኃይለማርያም
መቐለ ላይ በተካሄደ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ቂርቆስ ክፍለከተማን 2-1 በማሸነፍ የመጀመሪያ የሜዳ ላይ ድል አስመዝግቧል።
ተመጣጣኝ ፉክክር እና ማራኪ የኳስ ፍሰት በተስተዋለበት ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ ወደ ግብ ደርሰዋል ። የመቐለዋ ዮርዳኖስ ምዑዝ በመጀመርያው ደቂቃ ባደረገቻት ሙከራ የጀመረው ጨዋታው ግብ እስከተስተናገደበት 18ኛው ደቂቃ ድረስም በርከት ያሉ የጎል ሙከራዎች ያስመለከን ነበር። ከነዚህ ሙከራዎች ውስጥ የቂርቆስዋ ሠላም ለገሰ ከረጅም ርቀት ያደረገችው ሙከራ ለግብ የቀረበ እና የመቐለዋን ግብ ጠባቂ ምብራቅ አባዲ የፈተነ ነበር። ቂርቆሶች በ18ኛው ደቂቃ በሬዱ በቀለ ባስቆጠረቻት ግብ መምራት ቢጀምሩም መሪነታቸው የቆየው ግን ለሁለት ደቂቃዎች ነበር ፤ በሃያኛው ደቂቃ ላይ ሣሮን ሠመረ ከመስመር የተሻገረችላትን ኳስ ገጭታ በማስቆጠር ቡድኗን አቻ ማድረች ችላለች።
ሁለተኛው አጋማሽ ብዙም የግብ ሙከራ ባይታይበትም መቐለዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ ነበሩ። ሣሮን ሠመረ ባደረገችው መከራ ጥቃታቸው የጀመሩትት ባለሜዳዎቹ በ60ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ሙኡዝ ከርቀት ባስቆጠረችው ግሩም ግብ መሪ መሆን ችለዋል። በአንጻሩ ተዳክመው የታዩት ቂርቆሶች ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በመቐለዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሻሸመኔ ላይ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ እና አቃቂ ክፍለከተማ 1-1 ተለያይተዋል። ውጤቱ አቃቂዎች ከሦስት ተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ የተጋሩበት ሆኖም አልፏል።