በክረምቱ ወቅት የጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ በመሆን የተቀጠሩት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በልምምድ ሰዓት ላይ እየተገኙ አይደለም።
የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋር በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በርካታ ተስተካካይ ጨዋታዎች ቢቀሩትም አዳማ ከተማን ሲረታ ከሽረ ከሜዳው ውጪ ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል። ጅማ የሊጉ ሻምፒዮን በመሆኑ በአፍሪካ መድረክ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውም ጅቡቲ ቴሌኮምን በድምር ውጤት ከረታ በኃላ ባሳለፍነው አርብ በግብፁ አል አህሊ የ2-0 ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል። ሆኖም ከግብፅ መልስ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከቡድኑ ጋር እንደማይገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ቡድኑ ወሳኝ የመልስ ጨዋታ እያለበት አሰልጣኙ ያለመኖራቸው ጉዳይም አጠያያቂ ሆኗል። ዛሬ ክለቡ በ35 ሜዳ ልምምድ ሲሰራም አሰልጣኙ በሜዳ ላይ ያልተገኙ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ባገኘችው መረጃ መሠረት አሰልጣኙ የግል ጉዳይ ገጥሟቸው ከክለቡ ጋር ለጊዜው እንደማይገኙ የተነገረ ቢሆንም በአሰልጣኙ በኩል ካሉ ምንጮች ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ደግሞ አሰልጣኙ በክለቡ መሟላት የነበረባቸው በርካታ ጉዳዮች ስላልተሟሉላቸው እንደሆነ ልምምድ ማሰራት ያቆሙት ለመረዳት ተችሏል።
የፊታችን ዕሁድ ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ላለበት አባ ጅፋር የአሰልጣኙ ያለመኖር ተፅኖው ቀላል እንደማይባል መገመት አያዳግትም። ከቅርብ ወራት በፊት ከተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ውስብስ ችግሮች ውስጥ ገብቶ የነበረው ክለቡ አሁንም ከአል አህሊው ጨዋታ በፊት ከአሰልጣኝ ዘማርያም ጋር የተፈጠረውን ጉዳይ ፈር ማስያዝ ይጠበቅበታል።
በቀጣይ ሶከር ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተለች ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል ፡፡