በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የእግርኳስ ሜዳዎችን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ነገ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የመስክ ምልከታ ሊያደርጉ ነው።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በሆኑት ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራ አንድ ቡድን ነገ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የእግርኳስ ሜዳዎችን እንደሚጎበኝ ታውቋል። የአዲስ አባባ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለሰማዕት መርሀጥበብ እና የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለኢየሱ ፍስሀ (ኢንጂነር) እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን የሚያካትተው ይህ ጉብኝት ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ እንደሚካሄድም ታውቋል።
ቡድኑ በጉብኝቱ ከሚያካትታቸው የእግርኳስ ሜዳዎች መካከል ያለፉትን ሁለት ዓመታት በግንባታ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆመው እና አሁን ግንባታው ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሶ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የአበበ ቢቂላ ስታድየም አንዱ ሲሆን ለረጅም ጊዜያት ግንባታው ያልተጠናቀቀው እና አሁን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው የአቃቂ ስታድየምም ይገኝበታል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢምፔሪያል አካባቢ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረው እና እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ያልተጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ሊያስገነባው ያሰበው ስታድየም ከሚጎበኙት ውስጥ ሲካተት ጀሞ አካባቢ በቅርብ ዓመታት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስታድየምም የጉብኝት ሥነ ስርዓቱ አካል ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን የሚጎበኙ ሲሆን ምክትል ከንቲባው ከጉብኝቱ ባሻገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ አቅጣጫ ያስቀምጣሉም ተብሎ ይጠበቃል።