ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዞ የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ሰበታ ላይ ቡድናቸው ሰበታ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ የፈፀሙትን የዲሲፕሊን ግድፈት እና የቅጣት ዝርዝር ፌዴሬሽኑ እንደሚከተለው ገልጿል። ” የሰበታ ከተማ ቡድን አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ታኅሳስ 7 ቀን 2011 ሰበታ ከተማ ከ ፌዴራል ፖሊስ ካደረጉት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የዕለቱን ዳኞች አፀያፊ በመሳደብ እና ለመማታት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በጸጥታ አስከባሪዎች ሁኔታውን መቆጣጠር መቻሉ ሪፖርት ተደርጓል። አሰልጣኝ ክፍሌ ለሚመራቸው ተጫዋቾች አርዓያ መሆን ሲገባው ከስፖርታዊ ጨዋነት ድርጊት ውጪ በመሆን ለፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መምሪያ ” ክፍል 3፤ ምዕራፍ ሦስት፤ አንቀጽ 64፤ ንዑስ አንቀጽ 2መ ” መሠረት ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ ለ3 ወራት እንዲታገዱ እና 10,000 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል። ” ሲል አስታውቋል።
ከቅጣት ውሳኔ ጋር በተያያዘ የገላን ከተማው ኤፍሬም ቀሬ የተጋጣሚ ተጫዋች ሆን ብሎ በመማታት የ4 ጨዋታ እና 4,000 ሺህ ብር ቅጣት ሲተላለፍበት የወላይታ ሶዶው ፉዓድ መሐመድ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ አጸያፊ ስድብ በመሳደቡ ቀይ ካርድ የተመዘዘበት መሀኑ ሪፖርት በመደረጉ የ3 ጨዋታ እና 3,000 ብር ቅጣት ተላልፎበታል።