ሲዳማ ቡና በቀጣይ ሳምንት የሚያደርገው ጨዋታ የቦታ ለውጥ እንዲደረግበት ጠየቀ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ መርሐ ግብር ከሚደረጉ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይ የቦታ ለውጥ እንዲደረግ ሲዳማ ቡና ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብቷል፡፡ 

በቀጣዩ ሳምንት ሀሙስ ሶዶ ላይ እንዲከናወን የወጣው መርሐ ግብር በስፍራው ተገኝተን ማድረግ አንችልም የሚል ደብዳቤን ማስገባቱን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። ክለቡ በደብዳቤው ” በሁለቱ ክለቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት ባይሆንም ባለፉት ወራት በሲዳማ እና ወላይታ ዞኖች ተነስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ገና የሁለቱ ህዝቦች በእርቅ ሒደት ላይ ስላሉ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቶ ወደ ሠላማዊ መንገድ እስኪመጣ ድረስ ይህ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲደረግልን እንጠይቃለን።” የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ ነው ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው። ክለቡ በሁለተኛው ዙር የሚደረገው ጨዋታም የተጋጣሚን አድቫንቴጅ በጠበቀ መልኩ ከሀዋሳ ይልቅ አዲስ አበባ ላይ ቢደረግ የሚል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡ ተሰምቷል።