ነገ ከሚደረጉ የሰባተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ነው።
ከባህር ዳር በሽንፈት የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ድሉን ካሳካው አዳማ ከተማ ጋር ነገ 09፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይገናኛል። መልካም አጀማመር በማድረግ በሰንጠረዡ አናት ላይ እስከመቀመጥ ደርሶ ለነበረው ኢትዮጵያ ቡና ያለፉት ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በጥሩ እላለፉም። ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ በሦስቱ ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን በቻ ለማግኘት የተገደዱት ቡናማዎቹ በሜዳቸው ከሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ሰብስበው ወደ ቀደመው መንፈስ መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ሣምንት መቐለን ድል ያደረጉት አዳማዎች በበኩላቸው ከታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ወደ መሀሉ ተጠግተዋል። ድሉ ከሁለት የአቻ እና ከሁለት የሽንፈት ውጤቶች በኋላ የተገኘ እንደመሆኑም የቡድኑን አካሄድ ለማስተካከል የሚኖረው እገዛ ከፍ ያለ ከመሆኑም በላይ ለነገው ትልቅ በፊት መምጣቱ ለአዳማ መልካም የሚባል ነው።
አስራት ቱንጆን ብቻ በጉዳት የሚያጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የፊት አጥቂያቸው ሱለይማን ሎክዋ እና የመሀል ተከላካያቸው ወንድይፍራው ጌታሁን አገግመው ለነገው ጨዋታ እንደሚደርሱላቸው ተሰምቷል። በአዳማ በኩል የዐመለ ሚልኪያስ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ጉዳት አሁንም እንዳለ ሲሆን ሱራፌል ጌታቸው እና በመቐለው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ምኞት ደበበም በዚሁ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። ሆኖም ምኞት ለነገው ጨዋታ የመድረስ ዕድል ይኖረዋል።
የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ስብስብ የመጀመሪያ አሰላለፍ የማይተነበይ ሆኗል። ቡድኑ ውጤት ያጣባቸው ጨዋታዎች መነሻ ሊሆኑ ቢችሉም የአማኑኤል እና ሳምሶን በባህር ዳሩ ጨዋታ ተጠባባቂ መሆን ትኩረትን የሚስብ ነው። ቡድኑ ነገም በአሰላለፍ ረገድ ለውጦችን እንደሚያስመለክተን ቢገመትም ማጥቃትን መሰረት ያደረገ እና የግብ ዕድሎችን በቶሎ ለማግኘት በሚያስችል የመስመር ጥቃት ተጋጣሚውን ለማስጨነቅ እንደሚሞክር ይገመታል። በከንዓን ማርክነህ የሚመራው አዳማ ከተማ የመቐለውን ያህል ባይሆንም የማጥቃት አቀራረብ ይዞ እንደሚመጣ ቢጠበቅም አማካይ ክፍል ላይ ግን ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቀው መገመት አይከብድም። የከንዓን እና የበረከት ጥምረት የቡድኑን ጥቃት ወደ ግራ እንዲያደላ የሚያደርገው በመሆኑም ከኢትዮጵያ ቡና የቀኝ ወገን የተከላካይ ክፍል ጋር የሚኖሩውን ፉክክር ተጠባቂ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ካሉሻ አልሀሰንን የያዘው የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል ከኢስማኤል ሳንጋሪ እና አዲስ ህንፃ ጥምረት ጋር የሚያደርገው ትንቅንቅም ወሳኝ መሆኑ አይቀሬ ነው።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች 34 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 19 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አዳማ ከተማ 6 ጊዜ አሸንፏል። በ9 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይለዋል።
– 93 ጎሎችን ባስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት ኢትዮጵያ ቡና 62፣ አዳማ ከተማ 31 ጎሎችን አስቆጥረዋል። በ2002 ቡና 6-1 ያሸነፈበት ውጤትም ከፍተኛው ነው።
– አዲስ አበባ ላይ 18 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 14 ድል ሲያስመዘግብ አዳማ 2 አሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። የአዳማ ድሎች እና ሁለቱ አቻዎች የተገኙት ባለፉት 6 ጨዋታዎች ነው።
ዳኛ
– ጨዋታው ማኑኤ ወልደፃዲቅ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከባህር ዳር ከተማ ያገናኘውን ጨዋታ ከዳኘ በኋላ የሚመራው ሁለተኛ የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታው ይሆናል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
ዋቴንጋ ኢስማ
አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ተካልኝ ደጀኔ
ሳምሶን ጥላሁን – ዳንኤል ደምሴ – ካሉሻ አልሀሰን
አቡበከር ነስሩ – የኃላሸት ፍቃዱ – ሚኪያስ መኮንን
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ሮበርት ኦዶንካራ
ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሐመድ
አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ
ቡልቻ ሹራ – ከንዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ
ዳዋ ሁቴሳ