አንጋፋው የድሬዳዋ ስታዲየም ለወራት በማስፋፊያ እና በእድሳት ምክንያት ምንም ዓይነት ውድድሮችን ሳያስተናግድ ቢቆይም አብዛኛው የመጫወቻ ሜዳ ስራዎቹ በመጠናቀቃቸው የፕሪምየር ሊጉ ድሬዳዋ ከተማ የሜዳው ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የ1968 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የድሬዳዋ ስታድየም ለወራት የማስፋፊያ እና የመጫወቻ ሜዳ እድሳት ሲደረግለት በመቆየቱ ድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ የሜዳ ጨዋታዎቹን በሁለተኝነት ባስመዘገበው የሐረር ስታድየም እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። አሁን አብዛኛው የስታዲየሙ ማስፋፊያ እና የእድሳት ስራ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ እንዲሁም የመጫወቻ ሜዳው የተወሰኑ ሥራዎችን በቀሩት ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ ሜዳውን ለጨዋታ ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በተስተካካይ መርሐግብር የፊታችን ረቡዕ ከደቡብ ፖሊስ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በዚሁ ስታድየም እንደሚያደርግ ታውቋል።
በሌላ ዜና ድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ አዲስ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ በቅርቡ የሚሾም መሆኑን ሰምተናል።