በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና አቡበከር ናስሩ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ወደ ድል ተመልሷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህርዳር አቅንቶ ሽንፈትን ካስተናገደው የቡድን ስብስብ ውስጥ የኋላሸት ፍቃዱ ፣ ዳንኤል ደምሴ እና ሚኪያስ መኮንንን አስወጥተው በምትካቸው ሱለይማን ሎክዋ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አማኑኤል ዮሃንስን በተመተካት ወደ ጨዋታ ገብተዋል፡፡ በአንጻሩ በአዳማ ከተማዎች የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ካሳካው ቡድን ውስጥ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ መሰለፍ ባልቻለው ተከላካዩ ምኞት ደበበ ምትክ ቴዎድሮስ በቀለን ብቻ ቀይረው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ተሽለው በታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል ፤ አጋማሹ በርካታ ግለሰባዊ ስህተቶችም የታዩበት ነበር። በ10ኛው ደቂቃ ክሪዝስቶም ንታምቢ በጥሩ ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ካሉሻ አልሀሰን አንድ የአዳማ ተከላካይ ካለፈ በኋላ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስሩ እንዲሁም የአዳማው የመስመር አጥቂ በረከት ደስታ በተደጋጋሚ ቴዎድሮስ በቀለን እና ቶማስ ስምረቱን ጫና ውስጥ በማስገባት ስህተቶችን ለማሰራት ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለባቸው ቅፅበቶችም በርካቶች ነበሩ። በ21ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን ወደ ቀኝ በጣም ያደላውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ቢያሻማም በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ካሉሻ አልሀሰን በአስገራሚ ሁኔታ ሊያመክነው ችሏል ፤ በሰከንዶች ልዩነት አልሀሰን ካሉሻ በጥሩ መልኩ ያቀበለውን ኳስ ሉኩዋ ወደ ግብ ቢልካትም ሮበርት ኦዶንካራ አዳኖበታል፡፡ በመጀመሪያ አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ቡናዎች በተመሳሳይ በ38ኛው ደቂቃ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል በተዘናጉበት አጋጣሚ ካሉሻ ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ጥንቃቄን መርጠው ሲጫወቱ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ሦስቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ዳዋ ፣ ቡልቻ እና በረከትን በመጠቀም የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮችን ጫና ውስጥ በመክተት ስህተት እንዲሰሩ በማድረግ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ፤ በዚህም ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ውስጥ በተለይ ቶማስ ስምረቱ በተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲሰራ ተስተውሏል፡፡ በሰሞንኛ ተከታታይ ነጥብ መጣሎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደነበሩ ያስታውቁ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽም በእንቅስቃሴ ደረጃም ይህ ነው የሚባል የተሻለ ነገር ማሳየት አልቻሉም። በተመሳሳይ አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽም በጥንቃቄ አጨዋወት ነገር ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የከነዓን ማርክነህ መንቀሳቀስ ጋር ተዳምሮ በመልሶ ማጥቃት ከመጀመሪያው ተሽለው ቀርበዋል፡፡
በ54ኛው ደቂቃ ከጉዳት መልስ ወደ ቋሚ ተሰላፊነት የተመለሰው ሱሌይማን ሎክዋ ሁለት የአዳማ ተከላካዮችን አልፎ ወደ ግብ የላከው እና ሮበርት እንደምንም ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት አዳማዎች በ61ኛው እና በ72ኛው ደቂቃ አዲስ ህንጻ እና ዳዋ ሁቴሳ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ አክርረው ወደ ግብ የላኳቸው ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ ፤ ነገር ግን በቡድኑ የሁለተኛ አጋማሽ መሻሻል ውስጥ ቁልፍ የነበሩት ቡልቻ ሹራ እና ከነዓን ማርክነህ በጉዳት ከሜዳ ተቀይረው መውጣታቸውን ተከትሎ የቡድኑ መነሳሳት ሙሉ ለሙሉ ከስሟል ማለት ይቻላል፡፡
ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ከፍተኛ ጫና ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት የማሸነፍ ንጻሪያቸው በጣም ተዳክሞ ተስተውሏል፡፡
ነገር ግን በ87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሚኪያስ መኮንን ላይ ሱለይማን ሰሚድ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስሩ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ባለድል ማድረግ ችሏል፡፡በዚህም ኢትዮጵያ ቡና ሊጉ ከዕረፍት ከተመለሰበት ወቅት አንስቶ ከተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ መጣሎች በኃላ ወደ ድል መመለስ ችሏል።