በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ብቸኛ የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና አደማ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳክቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
” የውድድር ዘመኑን ጉዟችንን ዛሬ ጀምረናል፡፡” ዲዲዬ ጎሜስ- ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው…
” ጥሩ ጨዋታ ነበር ፤ ጨዋታውን ተቆጣጥረን መጫወት ችለናል፡፡ ደረጃ በደረጃ የጨዋታ መንገዳችንን እያጠራን እንገኛለን ፤ ከጨዋታው በፊት ለተጨዋቾቼ እንደነገርኳቸው ዛሬ አጫጭር ኳሶችን ለመጫወት አስበን ነበር የገባነው የተወሰኑ ስህተቶችን ብንሰራም በሂደት በርካታ በጎ ነገሮችን ማሳየት ችለናል፡፡ በሜዳው ላይ እኛ ብቻ ነበር የነበረነው ስለዚህ ማሸነፉ ይገባናል፡፡ ከባህር ዳሩ ሽንፈት በኃላ አስቸጋሪ ወቅቶችን አሳልፈናል የዛሬው ድልም ከዛ መንፈስ ለመውጣት ይረዳናል ፤ በአጠቃላይ የውድድር ዘመኑን ጉዟችንን ዛሬ ጀምረናል፡፡”
ስለ ሁለተኛው አጋማሽ የተጨዋቾች ቅያሬ እና ስለተጠቀሙት ቅርጽ…
“በቅያሬዎቻችን እንደ ሚኪያስ ዓይነት ተለዋዋጭ ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለማስገባት ሞክረናል ይህም ተሳክቶልናል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ከወትሮው በተሻለ መሀል ሜዳ ላይ በወጥነት መጫወት ችለናል፡፡ የአዳማ የመስመር ተከላካዮች እምብዛም የማጥቃት ባህሪ ስላልነበራቸው መስመሩ ላይ ሳንበዛ የተጠቀምነው የ4-1-3-2 ቅርፅ ውጤታማ አርጎናል፡፡”
“በሁለተኛው አጋማሽ በብዙ መልኩ ተሽለን ብንቀርብም በመጨረሻ ደቂቃ በተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈናል፡፡” – ሲሳይ አብርሃም- አዳማ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
” እንደተመለከታችሁት በመጀመሪያው አጋማሽ ክፍተቶች ነበሩብን በሁለተኛው አጋማሽ ግን በብዙ መልኩ ተሽለን ብንቀርብም በመጨረሻ ደቂቃ በተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈናል፡፡”
ስለተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት ምት…
” ውሳኔው የዳኛ ዕይታ ቢሆንም እንደእኔ ዕይታ ግን አያሰጥም ነበር ፤ ኳሱ ወደ መስመር እየሄደ የነበረ ኳስ ነበር ሲቀጥል ጥፋቱን ከሰራው ተከላካይ ጀርባ ሌሎች ተጫዋቾች ነበሩ። ስለዚህ የሚያሰጥ ኳስ አልነበረም፤ በሁለተኛው አጋማሽ እንደነበረን ብልጫ ግብም ማስቆጠር ይገባን ነበር ግን በነበረብን ያለመረጋጋት የተነሳ ነጥብ ልንጥል ችለናል፡፡”