የአሰልጣኝ አስተያየት | ” ቀድመው ጎል ሊያስቆጥሩብን እንደሚችሉ ገምተን ነበር ” አዲሴ ካሳ 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ስሑል ሽረን 6-1 በሆነ ውጤት ከረታ በኃላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች እንዲህ ብለዋል።

” ቀድመው ጎል ሊያስቆጥሩብን እንደሚችሉ ገምተን ነበር ” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ 

ስለጨዋታው

” ጥሩ ነበር ፤ የኛ እንቅስቃሴም ጥሩ ነዉ። እኛ የጠበቅነው የተቃራኒ ቡድን መከላከል ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ነበር። ይህም ብቻ አይደለም ቀድመው ጎል ሊያስቆጠሩብን እንደሚችሉም ገምተን ነበር። ሆኖም ጎልም ገብቶብን ቢሆን ያለን ነገር ጥሩ ነው። ምንአልባት ተጫዋች ባይወጣባቸዉ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር መሠለኝ። ግን ከዕረፍት በኋላ ያላቸዉን ሁሉ ነገሮች አውርደውታል። በዛም እኛ የተሻልን ነበርን።”

የደስታ ተጠባባቂ መሆን እና ቅያሪው

” ደስታ የጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ እግሩን ታሞ ነበር። የሰራውም መጨረሻውን ልምምድ ነበር። እሱንም የተሟላ አቋም ስላልነበረው የግድ ማስቀመጥ ነበረብን። ቅያሪውን ያደረግነው ራሱ ቦታ ላይ ነው። ይበልጥ ግን ደስታ ያንቦታ በደንብ ሸፋኖታል። መሀል ላይ እኛ እንደጠበቅነው አልነበረም ፤ እነሱ የመከላከል ጨዋታቸው ከፍተኛ ነበር። ስለዚህ ጨዋታችንን ዳር ላይ እና ፈጣን ማድረግ ነበረብን። ስለዚህ ደስታን ስናስገው። ማድረግ የፈለግነው በፍጥነት ወደ ተቃራኒ ክልል ውስጥ ማስገባት ነበር ስለዚህ እሱ እንደገባም ያን ነገር ነው የተገበርነው፡፡”

” እንደዚህ አይነት ዳኝነት አይቼ አላውቅም” በረከት ገብረመድህን – የስሑል ሽረ ረዳት አሰልጣኝ

ስለ ዳኛዉ  

”ኳስ በማዘግየት ብቻ ካርድ ይሰጣል፤ ሲሰድቡት ስንት ነገር ሲሉት ግን ካርድ ሊያሳያቸው አልቻለም። ሲጀመር እንደዚህ አይደለም ጨዋታ መቆጣጠር ያለበት። 45 ደቂቃ ባልሞላ ሰዓት ያወጣቸው ካርዶች አግባብ አይደሉም። ለራሱ ሳይረጋጋ ተጫዋቾች እንዴት ማረጋጋት ይችላል? ዳኞች ስለ ኢትዮጵያም እግርኳስ እድገት አስበው ፍትሀዊ ሆነው ማጫወት አለባቸው። በተጫዋቾች አዕምሮ ላይ ነው የተጫወቱት፤ እንደዚህ አይነት ዳኝነት አይቼ አላውቅም።

”ተጫዋቾች በሚረበሹበት ሰዓት እኛም እንደ ስታፍ ለማረጋጋት እየሞከርን ነበር። ነገር ግን የተጫዋቾች አዕምሮ ካልሰራ የኛ ስራ ብቻ በቂ አልነበረም። ዳኛው አዕምሮአቸውን ነው የጎዳው። ያደረገው ነገር ወዳልሆነ መንፈስ ነው የወሰደው። ጨዋታውን እያንዳንዱ እንቅስቃሴው ከመስመር ዳኛም ከማንም ጋር የሚናበብ ዳኛ አልነበረም። ጨዋታው ቀላል ነው፤ ማንም ዳኛ የሚዳኝው ነበር። ሀዋሳም ኳስ የሚጫወት ጥሩ ቡድን ነው፤ እኛም ኳስ ነው የምንጫወተው። ብዙ ግጭት የለውም፤ አንዳንዴ ጨዋታ ለዳኞች የሚከብዳቸው የሁለቱም ግጭት ያለው ጨዋታ ከሆነ ብቻ ነው።”

ስለ ቡድኑ ጉዞ እና ተጫዋቾች አጠቃቀም 

”ፕሪምየር ሊጉ ገና ነው። ማራቶን ማለት ነው ገና 6ኛ ጨዋታችን ነው። ግማሽ ዓመት እንኳን አልደረስንም። ሜዳችን ላይ የምንጥላቸው ነጥቦች በጣም ያሳስበናል። መያዝ ያለብንን አልያዝንም። ትልቁ አስቸጋሪ የሆነብን ነገር የተጫዋቾች ጉዳት ነው፤ 8 ተጫዋቾች ጉዳት አለብን። ሌላዉ ጥሩ በነበርንበት ሰዓት ግብ መድገም እንችል ነበር። ልደቱ ለማን ያልቀየርንበት ምክንያት እኛ ቦታችን ይዘን በመልሶ ማጥቃት ነበር መጫወት የፈለግነው። ሜዳቸው ስለሆነ ተጭኖ ለመጫወት ይከብደናል፤ ከዚህ አንፃር ነው።”