ሪፖርት | አፈወርቅ ኃይሉ ወልዋሎን በድጋሚ ታድጓል

ትግራይ ስታድየም ላይ በተደረገ የሊጉ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ ወልዋሎ በአፈወርቅ ኃይሉ የተጨማሪ ደቂቃ ግብ ደደቢትን 1-0 አሸንፏል።

09፡10 ላይ በጀመረው እና በርካታ የግብ ሙከራዎች በተስተናገዱበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በሰባተኛው ሳምንት በድሬድዋ ከተማ ከተሸነፈው ስብስባቸው ውስጥ አብርሃም ታምራት ፣ ሙሉጌታ ብርሃነ እና አለምአንተ ካሳን በኩማ ደምሴ ፣ አሌክሳንደር ዓወት እና እንዳለ ከበደ ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ ወልዋሎዎች በሜዳቸው ከድሬዳዋ አቻ ከተለያየው ስብስብ አብዱልራህማን ፉሴይኒን በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ፣ ብርሃኑ አሻሞን በአስራት መገርሳ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል። ከቡድኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥም ደስታ ደሙ ፣ ብርሀኑ ቦጋለ ፣ አስራት መገርሳ እና ኤፍሬም አሻሞ የቀድሞው ክለባቸውን ገጥመዋል።

ወልዋሎዎች በሚያደርጓቸው ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በርካታ የግብ ሙከራዎች ተስተናግደውበታል።
በተለይም እንየው ካሳሁን ከመስመር ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ኤፍሬም አሻሞ አክርሮ መትቶ መድሃኔ ብርሃኔ ተደርቦ ያወጣው እና በመጀመርያው ደቂቃ ለወልዋሎ በርካታ የግብ ዕድሎች ሲፈጥር የታየው አማኑኤል ጎበና በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥን ገብቶ አክርሮ ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት በቢጫ ለባሾቹ በኩል የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

በጨዋታው ለወልዋሎ የመስመር አጨዋወት በደምብ ተዘጋጅተው የመጡ የሚመስሉት ደደቢቶች ምንም እንኳን በማጥቃቱ በኩል አመርቂ ባይሆኑም የወልዋሎን የመስመር ጥቃት ለመመከት የተከተሉት አጨዋወት ከታሰበው በላይ ውጤታማ ነበር። ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾቻቸው አሌክሳንደር ዓወት እና እንዳለ ከበደ በመከላከሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከጥልቀት እየተነሱ እንዲጫወቱ ያደረጉት ደደቢቶች በተጋጣሚ ሜዳ የቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በወጣቱ አሌክሳንደር ዓወት ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። በተለይም ተጫዋቹ ከመስመር የተሻገረችለት ኳስ አክርሮ መትቶ አብዱልዓዚዝ ኬይታ በድንቅ ብቃት ወደ ውጪ ያወጣት እና ክዌክ ኢንዶህ በረጅሙ አሻምቶት በጭንቅላቱ ጨርፎ ያልተጠቀመባት አጋጣሚ በደደቢት በኩል ከተፈጠሩት ለጎል የቀረቡ ዕድሎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በጨዋታው ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ወልዋሎዎች በበኩላቸው የመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተለይም እንየው ካሳሁን ያሻማው ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ቅርብ ርቀት የነበረው ኤፍሬም አሻሞ ሞክሮ ወደ ውጪ ያወጣው እና አዶንጎ የደደቢት ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተጠቅሞ በግሩም ሁኔታ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ለኤፍሬም አሻሞ አሻግሮለት ኤፍሬም ከረሺድ ማታውሲ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝንቶ ቢመታም በማይታመን መልኩ ኳስ እና መረብ ሳያገናኙ ቀርተዋል።

በርካታ የሜዳ ላይ እሰጣ ገባዎች ባስተናገደው ሁለተኛ አጋማሽ ከመጀመርያ በአንፃራዊነት የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር የተስተዋለበት ነበር። ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከሳጥኑ ጠርዝ ባደረገው ሙከራ የጀመረው አጋማሹ በወልዋሎ በኩል በርካታ እጅግ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበት ነበር ፤ በተለይም ደስታ ደሙ ከመሃል ሜዳ አለፍ ብሎ ከርቀት አክርሮ መቶት ረሺድ ማታውሲ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣት ሙከራ ወልዋሎን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። አለምአንተ ካሳን ቀይረው ካስገቡ በኋላ በጥቂቱም ቢሆን በተጋጣሚ ሜዳ የነበራቸውን የቁጥር ማነስ መቀነስ የቻሉት ደደቢቶች በሁለተኛው አጋማሽ ብዙ ዕድሎች ባይፈጥሩም ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። ከነዚህም መሀከል አክዌር ቻሞ የወልዋሎ ተከላካዮችን አለመናበብ ተጠቅሞ መትቶት እንየው ካሳሁን ተደርቦ ያወጣው እና እንዳለ ከበደ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ብዙ የሜዳ ላይ ንትርኮች በታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ በ68ው ደቂቃ በክዌክ ኢንዶህ እና አፈወርቅ ኃይሉ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዶ ነበር። ጨዋታው ተቋርጦ ሲጀምርም ወልዋሎዎች ወደ ግብ ከመድረስ አልቦዘኑም። በሦስት አጋጣሚዎች ለጎል የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም ኳሶቹ በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው ጋናዊው ረሸድ ማታውሲን አልፈው መሄድ አልቻሉም። በተለይም ግብጠባቂው አብዱራህማን ፣ ፕሪንስ እና እንየው ከተመሳሳይ ቦታ አክርረው የሞከሯቸውን ኳሶች የመለሰበት መንገድ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ረጃጅም ኳሶች ምርጫቸው ያደረጉት ወልዋሎዎች ግን ሙከራቸው ተሳክቶ አፈወርቅ ኃይሉ ከመሃል ሜዳ አጋማሽ የተገኘችውን ቅጣት ምት በረጅሙ ሲመታው ኮከብ ሆኖ ባመሸው ረሽድ ማታውሲ እጅ ሾልካ ግብ በመሆን ወልዋሎን ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች። ግብ ከተቆጠረ በኋላ በወልዋሎ የቡድን አባላት ደስታ አገላለፅ ደስተኛ ያልሆኑት ደደቢቶች ከወልዋሎ ቡድን አባላት ጋር እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ድረስ የቆየ እሰጣ ገባ ፈጥረዋል። ጨዋታውም በ1-0 ውጤት የተገባደደ ሲሆን ደደቢቶች በሽንፈቱ ስሜታቸው በእጅጉ ተጎድቶ ከሜዳ ሲወጡ ተስተውለዋል።