አምበር ዋንጫ በዳሽን አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው 10ኛው የአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ ዛሬ በዳሽን ቢራ አሸናፊነት እና ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ተሸላሚነት ተጠናቋል፡፡

ከፍፃሜው በፊት 9፡00 ላይ በተደረገው የደረጃ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን አሸንፎ 3ኛ ደረጃ በማግኘት ውድድሩን አጠናቋል፡፡ ምንያህል ተሸመ እና ዳዋ ሁቴሳ(በፍፁም ቅታት ምት) የፈረሰኞቹን ግቦች ከመረብ ሲያሳርፉ ካርሎስ ዳምጠው የጦሩን ብቸኛ ግብ በጨዋታው መጨረሻ ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡

በፍፃሜው ተጋባዡ ዳሽን ቢራ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ ውድድሩን በበላይነት አጠናቋል፡፡ የዳሽንን የድል ግብ በክረምቱ አውስኮድን ለቆ ዳሽን ቢራን የተቀላቀለው ያሬድ ባዬ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፏል፡፡ ምንም እንኳን ዳሽን ቢራ ጨዋታውን ቢያሸንፍም በውድድሩ ደንብ መሰረት ተጋባዥ ቡድን ቻምፒዮን ቢሆን በፍፃሜው ተሸናፊው የአዲስ አበባ ክለብ የዋንጫው ባለቤት እንደሚሆን በማስታወቁ ኢትዮጵያ ቡና የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ ዳሽን ቢራ ደግሞ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ለአሸናፊዎች እና ኮከቦች ሽልማት የተሰጠ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡናው ዮሴፍ ዳሙዬ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እና ከመከላከያው መሃመድ ናስር ጋር በጣምራ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብርን በ4 ግቦች ተጎናፀፏል፡፡ የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው ተሸልመዋል፡፡

IMG_7657

ያጋሩ