በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት መቐለ 70 እንደርታ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉትን ብቸኛ የዕለቱ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ዛሬ 9፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ከአዳማ በሽንፈት የተመለሰው መቐለ ከተማ በሜዳው ከሀዋሳ ጋር ነጥብ የተጋራው ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል። ሁለቱ ቡድኖች በሻምፒዮንነት ፉክክር ውስጥ እንደሚኖሩ ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ይገመት የነበረ ቢሆንም ሁለቱም በተመሳሳይ አጀማመራቸው አላማረም። በተለይም ካሁኑ ሁለት ሁለት ጨዋታዎችን መሸነፋቸው ያልተጠበቀ ሆኗል። በንፅፅር የተሻለ አጀማመር የነበራቸው መቐለዎች ከዛሬው ጨዋታ በፊት ከሜዳቸው ውጪ በድቻ እና አዳማ ሲሸነፉ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሽረን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ አገገመ ሲባል ከቀጣዮቹ የሲዳማ እና ሀዋሳ ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ነበር። በመሆኑም የዛሬው ጨዋታ ለመቐለም ሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸነፊነት የመመለስ ግዴታ ውስጥ ሆነው የሚገናኙበት በመሆኑ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
መቐለ 70 እንዳርታ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው አርዓዶም ገብረህይወት በተጨማሪ በቀላል ጉዳት ምክንያት አንተነህ ገብረክርስቶስ እና ጋብሪል አህመድን ለነገው ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ጌታነህ ከበደ ፣ አሜ መሀመድ ፣ ምንተስኖት አዳነ እና መሀሪ መናም ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ጨዋታው ለሁለቱ ተጋጣሚዎች ያለው አስፈላጊነት ሲታይ ቡድኖቹ ግቦችን ለማስቆጠር በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን ይዘው እንደሚቀርቡ መገመት የሚቻል ቢሆንም በመከላከሉም ረገድ ጠበቅ ማለታቸው አይቀትም። በአዳማው ጨዋታ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሰብሮ የመግባት ችግር የተስተዋለባቸው መቐለዎች ዛሬ እጅጉን ተሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል። በተለይም ከአጥቂው ጀርባ የሚሰለፉት ሦስት አማካዮች ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለቡድኑ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል። በዚህም አማኑኤል እና ሳሙኤል በቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ተከላካዮች እና የመስመር ተመላላሾች መሀል ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ተጠባቂ ነው።
አጥቂዎቹን በጉዳት ሳቢያ ያጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ባለፈ በሌሎች የቡድኑ ክፍሎች ከሚገኙ ተጫዋቾቹም ግቦችን ማግኘት ይኖርበታል። በመሆኑም ከክፍት ጨዋታ ዘግይተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ከሚደርሱት አማካዮቹ የርቀት ሙከራዎች በተጨማሪ ከቆሙ ኳሶች የሚፈጠሩ ዕድሎች በፈረሰኞቹ በኩል ይጠበቃሉ። በሌላ በኩል የቡድኑ የመስመር ተመላላሾች እምብዛም ማጥቃት ላይ ከማይሳተፉት የመቐለ መስመር ተከላካዮች ጋር የሚያጋጣማቸውን ፍልሚያ በማለፍ ንፁህ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥሩ ተሻጋሪ ኳሶች ወደ ሳጥን ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– አምና በመጀመሪያው ሳምንት የተገናኙበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 1-1 የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ግንኙነታቸውም በተመሳሳይ ውጤት ተለያይተዋል።
– የመቐለው አማኑኤል ገብረሚካኤል በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ የምንተስኖት የመጨረሻ ደቂቃ ጎል በሁለተኛው ደግሞ የአብዱልከሪም ከርቀት ያስቆጥራት አስገራሚ ግብ የሚዘነጉ አይደሉም።
ዳኛ
– ከአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ዳኝቶ የነበረው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዚህ ጨዋታ ተመድቧል። ለሚ ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መስከረም ላይ ካደረጉት የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በኋላ የሚመራው የሀገር ውስጥ ጨዋታም ይሆናል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-4-3)
ፓትሪክ ማታሲ
አስቻለው ታመነ – ሳልሀዲን ባርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ
አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ– ኄኖክ አዱኛ
በኃይሉ አሰፋ – አቤል ያለው – አቡበከር ሳኒ
መቐለ 70 እነደርታ (4-2-3-1)
ፍሊፕ ኦቮኖ
ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ያሬድ ሀሰን
ዮናስ ገረመው – ሚካኤል ደስታ
አማኑኤል ገ/ሚካኤል – ኃይደር ሸረፋ – ሳሙኤል ሳሊሶ
ያሬድ ከበደ