“ከሜዳ ውጪ የተሸነፍንበት የጎል ልዩነት ተፅዕኖ ፈጥሮብናል፡፡” የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር (ምክትል አሰልጣኝ)

የጅማ አባ ጅፋሩ ምክትል አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ ተከታዮቹን አስተያየቶች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሰጥተዋል፡፡

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነው ፤ እኛም የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት ጥረት አድርገናል ፤ እነሱም እዛ ከነበራቸው ጨዋታ በመጠኑም ቢሆን የተለየ ነገር አድርገው ነው የሄዱት፡፡ በአንድ አጥቂ በመጠቀም ለመከላከል ሞክረዋል፤ እኛም ኳሱን ይዘን የተሻለ ነገር ለማድረግ ሞክረናል። ነገር ግን ከሜዳ ውጪ የተሸነፍንበት የጎል ልዩነት ተፅዕኖ ፈጥሮብናል፡፡”

ስለሜዳው

“እዚህ ሜዳ ላይ አንድ ቀን ለአንድ ሰአት ተኩል ያክል ነበር ልምምድ የሰራነው ፤ በሁለተኛው ቀን ቀለል ያለ ልምምድ ነበር የሰራነው። ሌሎች ሜዳዎች ላይ በግማሽ ሜዳ ነበር ልምምድ ስንሰራ የነበርነው ይህም በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ነበረው፡፡”

ስለዲዲዬ ለብሪ ረጃጅም ውርወራዎች

“የእኛ ተጫዋቾች የማዕዘን ምትም ሆነ የእጅ ውርወራዎችን በአጭር ተቀባብሎ እየቀነስን ለመሄድ ነበር ፍላጎታቸው ፤ ለዲዲየም እየነገርነው ነበር። በሳጥናቸው ውስጥ በዛ ብለው ስለሚገኙ ማድረግ የሚገባን ተጫዋቾችን እየቀነስን መሄድ ነበር። ነገርግን በዚህ ሂደት ውስጥ እሱ ደግሞ ኳሶችን በረጃጅሙ ይጥልና ያበላሽብነን ነበር፡፡”

ስለ አስቻለው የዘገየ ቅያሪ

“ሜዳ ውስጥ ከነበሩን የአጥቂ ተጫዋቾች በተሻለ ኳሶችን ያገኝ ነበር ፤ ቅያሬው አስቀድሞ የተዘጋጀ ነበር። ነገርግን አስቻለው የተሻለ ነገረ ይሰራል ብለን እስከመጨረሻው እየጠበቅን ነበር ፤ አስቻለው ብቻ አልነበረም ዲዲየንም ለመቀየር ተዘጋጅተን ነበር። ነገር ግን ካሉን ተጫዋቾች የተሻለ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው እነሱ ስለሆኑ ታግሰናቸዋል፡፡”